ቀጥታ፡

የጋምቤላ ክልልን ሰላም ለማስጠበቅ የጸጥታ መዋቅሩን ለማጠናከር እየተሰራ ነው

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 13/2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የውስጥና ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በመከላከል ሰላምን ለማስጠበቅ የጸጥታ መዋቅሩን የማጠናከር ስራ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

ክልሉ ሰፊ የድንበር ወሰን ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የውስጥና ድንበር ዘለል የጸጥታ ችግሮች ለመከላከል ዝግጅት ተደርጓል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኡቶው ኡኮት ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተለይም የበጋውን ወራት ተከትሎ የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጉሳ ድንበር ዘለል ዘርፊያዎችንና ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ሊፈጥሩ የሚችሉትን የጸጥታ ችግር ለመከላከል እየተሰራ ነው።

ራሱን የጋምቤላ ነፃነት ግንባር/ጋነግ/ ብሎ የሚጠራው የአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ተላላኪ እኩይ ሴራውን ለማምከን ጭምርም እንዲሁ።

የክልሉን የጸጥታ መዋቅር ለማጠናከር ብዛት ያላቸው የልዩ ኃይል የፖሊስ አባላትን ለማሰልጠን የምልመላ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በየደረጃው ለሚገኙ የሚሊሻ አባላትን አቅም በስልጠናና በግብዓት የማጠናከር ስራም እየተካሄደ መሆኑን  ምክትል ቢሮ ኃላፊው  አስረድተዋል።

ድንበር ዘለል የፈላታ አርብቶ አደሮች ከሚቀጥለው  ወር ጀምሮ የክልሉን ድንበር አቋርጠው በመግባት በባለሃብቶች እርሻ፣ በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክና በአካባቢው ማህበረሰብ የግጦሽ መሬት ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ችግር ለመከላከል ከወዲሁ ከወረዳዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

እነዚህ አካላት  ህገ -ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና ሌሎችን የወንጀል ችግሮችን ስለሚፈጥሩ ከወዲሁ ወደ ክልሉ እንዳይገቡ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግ ነው የተናገሩት።

በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለማግታት ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት የማህበረሰቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር አቶ ኡቶው ጥሪ አቅረበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም