ከህዝቡና ከሰራዊቱ ጋር በግንባር ተሰልፈን አሸባሪው ህወሃትን እንምክታለን - ኢዜአ አማርኛ
ከህዝቡና ከሰራዊቱ ጋር በግንባር ተሰልፈን አሸባሪው ህወሃትን እንምክታለን
ጎንደር ፤ ጥቅምት 13/2014 (ኢዜአ) የመንግስትን ሀገራዊ የክተት ጥሪ በመቀበል ከህዝባቸው ጎን በመሰለፍ የአሸባሪው ህወሃትን ወረራ እንደሚመክቱ ኢዜአ ያነጋገራቸው በጎንደር ከተማ የሚገኙ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ፡፡
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ፓርቲ /አብን/ የማእከላዊ ጎንደር ዞን አስተባባሪ አቶ ደሞዝ ካሴ እንደተናገሩት የህወሃት የሽብር ቡድን ወረራ ኢትዮጵያን የማፍረስና የመበተን ፕሮጀክት ነው።
የሀገር ሉአላዊነትና አንድነት ከቶም ለድርድር የሚቀርብ አለመሆኑ የፓርቲያቸው የፀና አቋም መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ በይፋ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ በሚል እየፈጸመ ያለውን ወረራ ለመቀልበስ ህዝቡና መንግስት እያደረጉ ያሉትን አኩሪ ተጋድሎ አብን በመደገፍ አባላቱንና አመራሮቹን ጭምር በማሳተፍ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
“የአማራ ህዝብ የሽብር ቡድኑ እየፈጸመበት የሚገኘውን ግድያ ዝርፊያና መፈናቀል እንዲቀጥል የሚፈቅድለት አይደለም” ያሉት አቶ ደሞዝ “ወረራውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቀልበስ ፓርቲው ከህዝብና ከመንግስት ጎን ተሰልፎ በተግባር እያረጋጠ ነው” ብለዋል።
ወታደራዊ እውቀት ያለው በውትድርና ገንዘብ ያለው በሀብቱ የአመራር ብቃት ያለው በመሪነት በመሳተፍ ሀገሪቱ የገጠማትን ፈተና በአሸናፊነት እንድትሻገር ፓርቲው የራሱን የታሪክ አሻራ በማሳረፍ ሀላፊነቱን በተግባር እንደሚወጣ ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያ በየዘመኑ የገጠሟትን የውጪና የውስጥ ፈተናዎች መሻገር የቻለችው በህዝቧና በመሪዎቿ ጥበብ ፣ጀግንነትና መስዋእትነት ነው"ያሉት ደግሞ የሰሜን፣ የማእከላዊና የደቡብ ጎንደር ዞኖች የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ/ኢዜማ/ አስተባባሪ ወይዘሮ እማዋይሽ አለሙ ናቸው።
"የህወሃት የሽብር ቡድን የውጪ ጠላቶቻችን ተላላኪ በመሆን ሀገር አፍርሶ እሺ ባይና አጎብዳጅ መንግስት ወደ ስልጣን እንዲመጣ አልሞ እየሰራ የሚገኝ የዘመኑ ባንዳ ነው" ሲሉ ገልጸውታል።
"ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለሀገር ሉአላዊነትና አንድነት በጋራ የምንቆምበት ጊዜ በመሆኑ ፓርቲያችን ከህዝቡ የተለየ አቋም የለውም"ብለዋል።
ፓርቲው በህልውና ዘመቻው አባሎቹንና አመራሮቹን ግንባር ድረስ በመላክ ከመንግስትና ከህዝቡ ጎን ተሰልፎ ሀገራዊ ግዴታውን እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
"ሀገር ከሌለ የህዝብም ሆነ የፓርቲዎች ህልውና አይታሰብም ያሉት ወይዘሮ እማዋይሽ ሀገር አፍራሾችን በማስወገድ ሀገርን ማስቀጠል ትውልዱ የተጣለበት ታላቅ ታሪካዊ ሃላፊነት ነው" ብለዋል።