በአገሪቱ የሚስተዋለውን ሥርዓት አልበኝነት ለማስቆም መንግሥት የሕግ ማስከበር ሥራን ማጠናከር አለበት-ምሁራን

78
አዲስ አበባ  ነሀሴ 12/2010 በአገሪቱ በአንዳንድ አከባቢዎች የሚስተዋለውን ሥርዓት አልበኝነት ለማስቆም መንግሥት የሕግ ማስከበር ሥራውን ማጠናከር እንዳለበት የሕግ ባለሙያዎችና ምሁራን ገለጹ። የተጀመረው አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ እንዳይቀለበስ ኅብረተሰቡ ከመንግሥትና ከጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት በመሥራት ኃላፊነቱን እንዲወጣም ሀሳብ ሰንዝረዋል። በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ደጀኔ ግርማ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች የሚስተዋሉት ሥርዓት አልበኝነት የሰው ህይወትን ህልፈት ዳርጓል። ያም ብቻ ሳይሆን የመንግሥትና የሕዝብ እንዲሁም የግለሰቦች ንብረት እንዲወድም በማድረግ በድምሩ የሰዎች ሰላም እንዲቃወስ በማድረግ አሉታዊ ጫና ማሳደራቸውን ነው የገለጹት። ይህ ዓይነቱ ድርጊት የሕገ-ወጥ ወይንም ሥርዓት አልበኝነት ምልክት መሆኑን የጠቀሱት መምህሩ መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራውን በተሟላ አኳኋን መሥራት አለበት ብለዋል። ህብረተሰቡም ወጣቶች ከምክንያታዊነት ውጪ በስሜት እንዲነዱ የሚያቀጣጥሉ አካላትን የማጋለጥና ለሕግ የማቅረብ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው ብለዋል። የሕግ ባለሙያው አቶ ዘፋንያህ ዓለሙ በበኩላቸው እንዲህ ያሉ የሥርዓት አልበኝነት ምልክቶች አንድ አገር የለውጥ ሂደት ውስጥ ስትገባ በአመዛኙ አይቀሬ ድርጊቶች ናቸው ይላሉ። ችግሮቹም አንድም መንግሥት ለሌሎች ጉዳዮች ቅድሚያ በማተኮር አልያም ደግሞ ህብረተሰቡ ለውጡን ሊያግዝ የሚችል በቂ ግንዛቤ ካለማዳበር ሊከሰት እንደሚችል ነው የጠቀሱት። ይሁንና መንግሥት ሕግን የማስከበር ሥራውን ከሁሉ በፊት በቀዳሚነት መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል። ሌላኛው የሕግና አስተዳደር ባለሙያና መምህር አቶ አሮን በትረወልድ ደግሞ ሕግና ሥርዓትን በዘለቂነት ለማስከበር ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ማጠናከር ተገቢ ነው ይላሉ። ይሁንና እነዚህ ተቋማትን ሥራቸውንና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፎቹ የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም እንዳለባቸው ባለሙያው ምክረ ኃሳብ አቅርበዋል። በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች በተከሰቱት ግጭቶች ምክንያት ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋል፤ በዚህም ለከባድ እንግልት ተዳርገዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም