ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ነገ በሚካሄዱ ተስተካካይ ጨዋታዎች ቀጥሎ ይውላል

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ነገ በክልል ከተሞች በሚካሄዱ ተስተካካይ ጨዋታዎች ቀጥሎ ይውላል። ፕሪሚየር ሊጉ ከሁለት ሳምንታት መቋረጥ በኋላ ግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም በተስተካካይ ጨዋታዎች መጀመሩ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ዳኞች እና ታዛቢዎች ማህበር 'ዳኞች ለሶስት ሳምንታት ማንኛውንም ውድድር እንደማይዳኙ በመግለጽ የአቋም መግለጫ ማውጣቱን' ተከትሎ የሊጉ ጨዋታዎች ተቋርጠው ቆይተዋል። ፌዴሬሽኑ ከማህበሩ ጋር ግንቦት 2 ቀን 2010 ዓ ም ባደረገው ውይይት ፕሪሚየር ሊጉ እንዲቀጥል ስምምነት ላይ በመደረሱ ሊጉ በተስተካካይ ጨዋታዎች ጀምሯል። በዚህም መሰረት ነገ በድሬዳዋ ስታዲየም ድሬዳዋ ከተማ ከወላይታ ድቻ እና  መቐለ ላይ መቐለ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በ19 ነጥብና በአምስት የግብ እዳ በፕሪሚየር ሊጉ ግርጌ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ድሬዳዋ ከተማ የነገው ጨዋታ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በጣም ወሳኝ ነው። በስምኦን አባይ የሚሰለጥነው ድሬዳዋ የሜዳውን ባለቤትነት ተጠቅሞ ማሸነፍ ከቻለ ሌሎቹ ቡድኖች እስኪጫወቱ ድረስ ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ይችላል። በአንጻሩ በዘነበ ፍስሐ የሚሰለጥነው ወላይታ ድቻ 27 ነጥብ ይዞ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ነገ ማሸነፍ ከቻለ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ወደ መሪዎቹ መጠጋት ይችላል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በ36 ነጥብ ሁለተኛ መቐለ ከተማ በ35 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን የነገው ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች እጅግ ወሳኝ ነው። ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የመጣውና በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው መቐለ ከተማ በሊጉ አስገራሚ የሚባል ግስጋሴ እያደረገ ይገኛል። ጋናዊው የክንፍ ተጫዋች ቢስማርክ ጋይስ፣ የቡድኑ አምበል ሚካኤል ደስታና የክንፍ ተጫዋቹ አማኑኤል ገብረሚካኤል ለቡድኑ ውጤት ቁልፍ ሚና እየተወጡ ይገኛሉ። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ወደ ማሸነፍ የመጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ የነገው ጨዋታ ወደ ዋንጫ ለሚያደርገው ግስጋሴው ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ነው። በፖርቹጋላዊው ማኑኤል ቫዝፒንቶ የሚሰለጥነው ቅዱስ ጊዮርጊስ የውድድር ዓመቱ ሲጀመር ከነበረው ደካማ አጀማመር በመውጣት በአሁኑ ሰአት በጥሩ የማሸነፍ ስነልቦና ላይ ይገኛል። የፕሪምየር ሊጉ መደበኛ መርሃ ግብሮች ረቡዕ ግንቦት 15 ቀን በሚካሄዱ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ጅማ አባጅፋር ፕሪምየር ሊጉን በ39 ነጥብ ሲመራ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና አዳማ ከተማ በተመሳሳይ 36 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የጅማ አባ ጅፋሩ ናይጄሪያዊ ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ በ14 ጎሎች ሲመራ፣ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደና የአዳማ ከተማው ዳዋ ሁቴሳ በተመሳሳይ ዘጠኝ ግቦች ይከተላሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም