የመረጠንን ህዝብ አደራና ሀላፊነት ለመወጣት በቁርጠኝነት እንሰራለን - ኢዜአ አማርኛ
የመረጠንን ህዝብ አደራና ሀላፊነት ለመወጣት በቁርጠኝነት እንሰራለን
ሐረር ፤ ጥቅምት 12/2014 (ኢዜአ) የህብረተሰቡን ጥያቄዎች የሚመልሱ ተግባራትን በማከናወን የመረጣቸውን ህዝብ አደራና ሀላፊነት በብቃት ለመወጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።
በዛሬው የክልሉ መስራች ጉባኤ በድጋሜ እንዲያገለግሉ የተሾሙት ርዕሰ መስተዳድሩ ባደረጉት ንግግር ፤ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራትን ለማከናውን ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በክልል ደረጃ በተጀመረው ስር ነቀል ለውጥ ሂደት ላይ የታዩ ጥንካሬዎችን በማጎልበትና ክፍተቶችን በማስተካከል ህዝቡ የሚጠብቀውን በእኩልነት ላይ የተመሰረት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በህዝቦች እኩልነት፣ የጋራ ተጠቃሚነትና አንድነት ላይ የተመሰረተ መዋቅራዊ ለውጥ ለማረጋገጥ በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች በሚካሄዱት ተከታታይ እንቅስቃሴዎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችን እና የክልሉ ነዋሪ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ትርጉም ባለው ሁኔታ ተሳታፊ ለማድረግ ይሰራል ነው ያሉት አቶ ኦርዲን።
"በአሁኑ ወቅት የሀገርን ሉዓላዊነትና አንድነት ለመጠበቅ የሚደረገው ተጋድሎ በላቀ አንጸባራቂ ድል ለማጠናቀቅ የተጀመረውን ደጀንነትና አጋርነነት ይበልጥ በማጠናከር አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ ያለእረፍት እንሰራለን" ብለዋል፡፡
የክልሉን አርሶ አደር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በተለይም የወጣቶች፣ የሴቶችና የአጠቃላይ የህዝቡን ሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ችግር ትርጉም ባለው መልኩ ለመፍታት በተጨባጭ ጥናት ላይ የተመሰረቱ ተከታታይ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
አመራር ቢለዋወጥ የማይዛነፍ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ፣ ለሰላም፣ ለልማት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለህዝባችን መብት መረጋገጥ ዘብ የሚቆም የጸጥታ መዋቅርና ኃይል ለመገንባት የተጀመሩ ተግባራትም ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ህገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታን እንዲሁም ሌብነትን በቁርጠኝነት ለመከላከል ቆራጥ እርምጃ እንደሚወሰድ ነው ርዕሰ መስተዳደሩ የገለጹት።
የምክር ቤት አባላትና በተለያዩ የሀላፊነት ደረጃ የሚገኘው አመራር እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ህዝብ የጣለባቸውን አደራ እንዲወጡና ለገቡት ቃል እንዲታመኑም መልዕክት አስተላልፈዋል።