ቀጥታ፡

የአፍሪካ ቀንድ የኢነርጂ ትስስር የቀጠናውን እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል

ጥቅምት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ ቀንድ የኢነርጂ ትስስር የቀጠናውን እድገት በላቀ ደረጃ እንደሚያጠናክረው ተመላከተ።

በ’ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሸቲቭ’ ስር የሚደረገው የኃይል አቅርቦት ትስስር በታዳሽ ሀይል ሀብት የተሞላችውን ኢትዮጵያን ከመጥቀም ባሻገር የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግራቸው በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ለግሎባል ታይምስ ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲና ሱዳን እየተዘረጋ ያለው ከፍተኛ የሃይል ማስተላለፊያ መስመር ሲጠናቀቅ ቀጠናዊ የኃይል ትስስር ከመፍጠሩ ባለፈ የጋራ ልማትን እንደሚያፋጥን አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቻይና የኃይል አቅራቢ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር ከፍተኛ የኃይል እጥረት ላለባቸው የጎረቤት ሀገራት ኃይል የሚያስተላልፈውን መስመር በስኬት በማጠናቀቅ የጋራ ተጠቃሚነትን ታረጋግጣለች ብለዋል፡፡"ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለመላክ ከኬኒያና ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር ስምምነት ተፈራርማለች ”ሲሉ ነው አምባሳደር ተሾመ ያስታወሱት፡፡

"ይህን የምናደርገው በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ራሳችንን ችለን ሳይሆን ያለንን ሃብት ከጎረቤቶቻችን ጋር መካፈል ለቀጣናዊ ትስስር በጣም ጠቃሚ መሆኑን በመረዳታችን ነው ” ብለው የህዳሴ ግድቡ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ሞተር ከመሆን ባለፈ በአህጉሪቱ የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ሽግግር ልዩ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት በግዙፍ ፕሮጀክት ግንባታዎች የታጀበ ሲሆን ከነዚህ መካከል የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡አዳማ አንድ 51 ሜጋ ዋት እና አዳማ ሁለት 153 ሜጋ ዋት የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች እንዲሁም የተከዜ 300 ሜጋ ዋት የኃይል ማመንጫ የቻይና ወዳጅነት አሻራ ያረፈባቸው ስራዎች ናቸው፡፡

ለኢትዮጵያ አዲስ ተስፋ የዘራው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡"በኢትዮጵያ ሰፊ የሆነ የኃይል አቅርቦት ምንጭ አለን፤ ከነዚህ መካከል በርካታዎቹ ሃብቶች የንፋስ፣ የፀሃይ፣ የውኃ፣ የእንፋሎት ኃይል ማመንጨት የሚችሉና ያልተነኩ ታዳሽ የሃይል ሃብቶች ናቸው” ብለዋል አምባሳደሩ፡፡

ኢትዮጵያ በአህጉራዊ ትብብርና ትስስር በጽኑ የምታምንበት ዋናው ምክንያት መፃኢ እድላችንን በጋራ በመወሰን አብረን መኖር እንደምንችል በመገንዘቧ ነው ብለዋል፡፡ቻይና ለቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሸቲቭ ከያዘችው ኢንቨስትመንት ውስጥ 40 በመቶው ለኃይል አቅርቦት ትስሰር በማዋል በፍጥነት እድገት ማሳየቱ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም