በአዲስ አበባ የአየር ብክለትና የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት እየጨመረ ነው

ጥቅምት 09/2014 /ኢዜአ/   በአዲስ አበባ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስና የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ሊከናወኑ ነው።

በአፍሪካ በተመረጡ 13 ትላልቅ ከተሞች የሚተገበረው የአየር ንብረት ትግበራ የአዲስ አበባ እቅድ በዛሬው እለት ይፋ ሆኗል።

እቅዱ በሰባት የአፍሪካ ከተሞች ላይ ቀደም ብሎ ይፋ መደረጉ ተገልጿል።

የሲፎርቲ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ጊፍቲ ናዲ እንዳሉት የትግበራ እቅዱ  እ.አ.አ በ2015 ይፋ የሆነውና የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት መቀነስ ላይ የሚያተኩረው የፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት የከተሞች እቅድ አካል ነው።

በሲፎርቲ የተመረጡ 13 የአፍሪካ ከተሞች መኖራቸውንና ከዚህ ቀደም አክራ ፣ ደርባን ፣ጆሃንስበርግን ጨምሮ በስድስት ከተሞች እቅዱ ይፋ መደረጉንም አስታውሰዋል።

የትግበራ እቅዱ ከተሞች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል መስራት ያለባቸውን ተግባራት የሚለዩበት መሆኑንም ገልፀዋል።

በእቅዱ በመታገዝ የተለዩ ተግባራትን በአምስት አመት እውን ለማድረግ እንደሚሰራም ጊፍቲ    አንስተዋል።

ለእቅዱ ትግበራ የተመረጡት ከተሞች ከ3  ሚሊዮን ህዝብ በላይ የያዙና የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመከላከል በቁርጠኝነት የሚሰሩ አመራሮች ያሏቸው መሆናቸውንም አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን የአየር ንብረት ለውጥ ማካተት ቡድን መሪ ፋንቱ ክፍሌ፤ በከተማዋ እ.አ.አ. በ2012 እና 2016  በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በከተማዋ የአየር ብክለትና የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት እየጨመረ ይገኛል።

በከተማዋ በተመረጡ ቦታዎች በተሰበሰበ የመኪና ጭስ ልኬት መረጃ መሰረት የጋዝ ልቀት እየጨመረ መምጣቱን አሳይቷል ብለዋል።

በከተማዋ የተጋላጭነት ዳሰሳ ጥናት መደረጉን ጠቅሰው የትግበራ እቅዱ እነዚህን መረጃዎች መነሻ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የትግበራ እቅዱ ኮሚሽኑ ከሲፎርቲ ጋር በመሆን ያዘጋጀውና ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሊተገበሩ የሚገቡ  34 ተግባራትን ያካተተ መሆኑንም ገልፀዋል።

ከተግባራቱ መካከል በኢንዱስትሪዎች በቴክኖለጂ የታገዘ ኢነርጂ መጠቀም፣ የአረንጓዴ ሽፋን ማሳደግ፣ የደረቅ ቆሻሻን አስተዳደርንና የነዳጅ ጥራትን ማስጠበቅና አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚገኙበትም ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በእቅዱ የተዘረዘሩትን ተግባራት በስራዎቻቸው አካተው እንዲተገብሩ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም