ቀጥታ፡

በአሸባሪው ህወሓት ላይ ጠንካራ እርምጃ በፍጥነት መውሰድ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ ጥቅምት 11/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ /ኢሕአፓ/ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሳውን አሸባሪው ህወሓት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ጠየቀ።

ኢሕአፓ መሪ አቶ ገብረወልድ ወልደሰንበትን ጨምሮ ሌሎች አመራር አባላት በተገኙበት ዛሬ ይፋ ባደረገው የአቋም መግለጫ የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ በጥልቀት መርምሪያለሁ ብሏል።

አሸባሪው ህወሃትና ሌሎች ፀረ-ሕዝብ ኃይሎች ከባዕዳን ጠላቶች ጋር በማበር በከፈቱት ጦርነት በአማራ፤ በአፋር፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ተፈናቅሎ እየተሰቃየ ነው።

የአሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰው የክህደት ጭፍጨፋ የመጀመሪያ እንዳልሆነ የገለጸው ኢህአፓ፤ ይህ የሽብር ድርጅት ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሚያደርጋቸው ከእኩይ መገለጫዎቹ አንዱ መሆኑን አብራርቷል።

በ1967 ዓ.ም የኢሕአፓ መሥራች በትግራይ አሲምባ ይንቀሳቀስ በነበረበት ወቅት አሸባሪው ሕወሃት ፀረ- ኢትዮጵያ አቋም ያለው መሆኑን በመረዳቱ ሲታገለው መቆየቱን አስታውሷል።

አሸባሪው ህወሃት አብያተ ክርስትያንና መስጊዶች ላይ ያደረሰው ጥቃትን አውግዞ፤ "ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደዚህ ዓይነት አስነዋሪ ነገር አጋጥሟት አያውቅም" ብሏል።

መንግስት አሸባሪው ህወሃት ባለበት አካባቢ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን ከጥፋት እንዲጠብቅ ለአማኞችና ለቤተ-እምነቶችም ከፍተኛ ጥበቃ እንዲያደርግ ጠይቋል።

የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብሮ የቆመ መሆኑን ጠቁሞ፤ ከመሠረቱ እንዲነቀል በማንኛውም መልክ ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ አሸባሪው ህወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማምከን ቁርጠኝነቱን ያሳየ መሆኑን ጠቁመው፤ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ሆኖ ወሳኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

በሕልውና ዘመቻው አሸባሪዎቹን ህወሓትና ሸኔ ለመደምሰስ የተጀመረው ትግል መንግሥት በቁርጠኝነት አጠንክሮ እንዲቀጥል ፓርቲው እንደሚደግፍ በመግለጫው አመልክቷል።

በመሆኑም መንግሥት ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለመጨረስ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስድ የጠየቀው ኢህአፓ፤ ችግር ውስጥ ያለውን ህዝብ እንዲታደግ ብሎም ለተፈናቃይ ወገኖች ዕርዳታ አቅርቦትም እንዲያጠናክር ጠይቋል።

የውጭ ኃይሎች በተለይም ምዕራባውያኑ በዕርዳታ ስም የአሸባሪው ህወሓትን በሎጅስቲክስ፣ በስንቅና ትጥቅ እያገዙ ስለመሆናቸው መረጋገጡን አስታውሷል።

ስለሆነም መንግሥት በተራድዖ ስም የገቡ የአሸባሪው ህወሓት ድጋፍ አቅራቢ የነበሩ ተቀጣሪዎችን ማባረሩ "አግባብነት ያለውና ትክክለኛ አቋም ነበር" ነው ያለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም