ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ጉዳይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲይዝ የማድረግ ተግባር ይጠናከራል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ወቅታዊ የውስጥ ጉዳይ ላይ ትክክለኛ መረጃ የሌላቸውን አገራት የማስረዳት ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

 የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከቀናት በፊት ባካሄዱት ወርሃዊ ስብሰባቸው በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መምክራቸው ይታወሳል።

በስብሰባቸውም በኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰው ግጭት እንደሚያሳስባቸውና በሰብዓዊ እርዳታ ዙሪያና መፍትሄ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

እርምጃውም የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽንና የመንግሥታት ድርጅት በጋራ የሚያወጡትን ሪፖርት ተከትሎ የሚወሰድ መሆኑን ኅብረቱ አስታውቋል።

በስብሰባውም በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲወሰድ የሚፈልጉና የማይፈልጉ ሁለት ጎራዎች መፈጠራቸውን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የተናገሩት።

ይህንንም ከግምት በማስገባት ከኢትዮጵያ ጎን የሚቆሙትን አገራት አብረው እንዲዘልቁ ወዳጅነትን የማጠናከር ሥራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በተለይም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በቂ መረጃ የሌላቸውንም አካላት የማስረዳትና የማስገንዘብ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።   

አንዳንድ የውጭ ሃይሎች የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እርስ በእርሱ የሚጣረስ መርህ የሚከተሉ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንንም ማረምና ማስተካከል እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት።

በተለይም አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበና የሐሰት መረጃ የማስተላለፍ ሥራ ላይ ተጠምደው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ይህንንም ለማስተካከል በተለይም ትክክለኛ መረጃዎችን የማቀበል ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በተለይም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው በውጭ ያለው ዲያስፖራም የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ጠቁመዋል።  

በእስካሁኑ ሂደትም ዲያስፖራው ከሚሲዮኖች ጋር በመተባበር የአገሪቷን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉንም ተናግረዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ ኅብረቱ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን የልማት ድጋፍ በተመለከተም ውይይት አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም