ቀጥታ፡

በፊፋ ወርሃዊ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ በሶስት ደረጃዎች ዝቅ ብላለች

አዲስ አበባ ጥቅምት 11/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) በወንዶች ወርሃዊ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ በሶስት ደረጃዎች ዝቅ ብላ 137ኛ ደረጃ ላይ ስትሆን በሴቶች ደግሞ 112ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) የጥቅምት ወር የዓለም የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ ዛሬ ይፋ አድርጓል።

በዚህም ኢትዮጵያ በመስከረም ወር ከነበረችበት 134ኛ ደረጃ ሶስተኛ ደረጃዎችን ዝቅ ብላ 137ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

በኳታር በሚካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ ዞን በሚካሄደው የማጣሪያ ጨዋታ በምድብ ስምንት የሚገኘው የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ 3 ለ 1 እና 1 ለ 0 መሸነፉ የሚታወስ ነው።

ብሔራዊ ቡድኑ ቀጣይ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን በሕዳር ወር 2014 ዓ.ም ከጋና እና ዚምባቡዌ ጋር ያደርጋል።

በወንዶች የእግር ኳስ ደረጃ ሴኔጋል ከዓለም 20ኛ ከአፍሪካ ደግሞ አንደኛ ደረጃን ይዛለች።

ቱኒዚያ ከዓለም 27ኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ፣ ሞሮኮ ከዓለም 29ኛ ከአፍሪካ ሶስተኛ፣ አልጄሪያ ከዓለም 30ኛ ከአፍሪካ አራተኛ እና ናይጄሪያ ከዓለም 36ኛ ከአፍሪካ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ቤልጂየም አንደኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ብራዚል፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያንና እንግሊዝ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዝ ችለዋል።

አውሮፓዊቷ አገር ሳን ማሪኖ በእግር ኳስ የደረጃ ሰንጠረዥ 210ኛ በመያዝ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች።

በሴቶች የፊፋ ወርሃዊ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ ደግሞ ኢትዮጵያ በመስከረም ወር በነበረችበት 112ኛ ደረጃ ቀጥላለች።

በ2022 በሞሮኮ በሚካሄደው 12ኛው የአፍሪካ የሴቶች የእግር ኳስ ዋንጫ ለመሳተፍ ትናንት በሴንት ሜሪ ስታዲየም ከዩጋንዳ አቻው ጋር ባደረገው የማጣሪያ ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) 2 ለ 0 መሸነፉ ይታወቃል።

ብሔራዊ ቡድኑ የመልስ ጨዋታውን ጥቅምት 16 ቀን 2014 ዓ.ም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያደርጋል።

በፊፋ የሴቶች ወርሃዊ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ ናይጄሪያ ከዓለም 38ኛ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ካሜሮን ከዓለም 52ኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ፣ ደቡብ አፍሪካ ከዓለም 55ኛ ከአፍሪካ ሶስተኛ፣ ጋና ከዓለም 60ኛ ከአፍሪካ አራተኛ ኮትዲቭዋር ከዓለም 61ኛ ከአፍሪካ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ከዓለም አገራት በሴቶች አሜሪካ የመጀመሪያውን ደረጃ ስትይዝ፤ ስዊድን፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድና ፈረንሳይ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

አፍሪካዊቷ ሞሪሺየስ 168ኛ በመሆን በሴቶች የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም