ቀጥታ፡

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በጤናው ዘርፍ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል

አዲስ አበባ ጥቅምት 11/2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጤናው ዘርፍ ውጤታማ ስራ መከናወኑ ተገለጸ።

በአዲስ አበባ በጤናው ዘርፍ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላከናወኑ ወጣቶች ጤና ሚኒስቴር እውቅና ተሰጥቷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ፤ በዘንድሮው ክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለይም በጤናው ዘርፍ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ህሙማንን በመንከባከብ፣ ታካሚዎችን በተለያየ መልኩ እገዛና ድጋፍ በማድረግ የነበራቸው ሚና የጎላ ነበር ነው ያሉት።

የበጎ ፈቃድ ስራ በገንዘብ የማይገዛ ነገር ግን በርካታ ስራዎች እየተሰሩበት ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በጎ ተግባር መሆኑን ዶክተር አየለ ተናግረዋል።

የበጎ ፍቃድ ስራ ሰዎችን ያለገንዘብ ክፍያ በመርዳት የህሊና እርካታ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው የሰዎች ጥሩነትና ደግነት የሚገለጽበት በመሆኑ "በዚህ ተግባር የተሳተፋችሁ ወጣቶች ልትኮሩ ይገባል" ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመሆኑም የበጎ ፈቃድ ስራ የአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ዘላቂነት ኖሮት ወገኖቻቸውን በሁሉም መስክ በማገዝ ወጣቶች እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

እውቅና ከተሰጣቸው በጎ ፈቃደኞች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች ዜጎችን በነፃ በማገልገላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በጤናው ዘርፍ የኮሮናቫይረስ ፈታኝ የሆነበት ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው በየጤና ተቋማቱ ታካሚዎችን በተለያየ መልኩ ማገዝ ችለናል ብለዋል።

በሆስፒታል ግቢ ፅዳት፣ በተለይም አዳዲስ ታካሚዎች አገልገሎት እንዲያገኙ መረጃ መስጠትና ቦታ ማመላከት እንዲሁም በመንከባከብ ወጣቶቹ በነፃ ማገልገላቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም