የቤተክርስቲያኗ ወርሃዊ የጡረታ አበል ክፍያ ቅሬታን አስከትሏል - ኢዜአ አማርኛ
የቤተክርስቲያኗ ወርሃዊ የጡረታ አበል ክፍያ ቅሬታን አስከትሏል
አዲስ አበባ ነሀሴ 12/2010 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለረጅም ዓመታት ያገለገሉና በጡረታ የተገለሉ የቀድሞ የአስተዳደር ሠራተኞች "የሚከፈለን ወርሃዊ የጡረታ አበል አነስተኛና የወቅቱን የኑሮ ሁኔታ ያገናዘበ ባለመሆኑ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግር ተዳርገናል" አሉ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ ቤተክርስቲያኗ ቋሚ በጀት የሌላት በመሆኑ የአቤቱታ አቅራቢዎቹን ጥያቄ ለማስተናገድ መቸገሩን ገልጿል። ቅሬታቸውን ለኢዜአ ያቀረቡት በመንበረ ፓትሪያርክ ጽህፈት ቤት በተለያዩ የሥራ መደቦች በቋሚነት ከ20 እና 30 ዓመታት በላይ ማገልገላቸውን ይገልፃሉ። አቤቱታ አቅራቢዎቹ በጡረታ ከተገለሉ በኋላ የሚከፈላቸው ወርሃዊ የጡረታ አበል ወቅታዊ የኑሮ ውድነት ሁኔታውን ያገናዘበ ባለመሆኑ "ቤተክርስቲያኗ ጭማሪ እንድታደርግልን ብንጠይቅም ምላሽ ሊሰጠን እልተቻለም" ብለዋል። መንግስት የኑሮ ውድነትን መሰረት አድርጎ ከሐምሌ 2006 ዓ.ም ጀመሮ የደመወዝ ጭምሪ ያደረገ ቢሆንም በቤተክርስቲያኗ ለረጅም ዓመታት ስናገለግል የቆየን ጡረተኞች ግን ጭማሪ ሳይደረግልን በመቆየታችን ከጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጅ እስከ ቅዱስ ፓትሪያርኩ ድረስ አቤቱታ ቢናቀርብም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም ይላሉ። ቅሬታቸውን ከገለጹት መካከል በኩረ ትጉሃን ዓለም አታላይ እንዳሉት"በዚህ ተቋም ውስጥ ጠቅላላ በሀገሪቱ ከማዕከል እስከ ታች ወረዳ ድረስ ከ3 መቶ በላይ ጡረተኞች አለን፤ እነዚህ ጡረተኞች ምንም ነገር እስከ አሁን ጭማሪ አላገኘንም˝ ብለዋል። ብዛታችን ከ300 ይበልጣል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ በዚህ ሳቢያ የኑሮ ውድነቱን ማሸነፍ ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግር መዳረጋቸውን በመግለጽ ከመካከላቸው አንዳንዶችም መታከሚያና የእለት ጉርስ በማጣት ህይወታቸው ያለፈ ጓደኞቻቸው መኖራቸውንም በምሬት ገልፀዋል። በቤተክርስቲያኗ የመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት የህግ አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ አፈ መንበር አባ ገብረስላሴ ጌትነት፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጉዳዩን ከዚህ ቀደም ወደ ፍርድ ቤት ይዘው በማምራት ክስ ቢያቀርቡም ጥያቄያቸው ተቀባይነት አለማግኘቱን ገልፀዋል። ቤተክርስቲያኗ በራሷ በጀት የምትተዳደር እንደመሆኗ መጠን የአቅም ውስንነት ያለባትና ቋሚ በጀት የሌላት በመሆኑ ጥያቄያቸውን ለማስተናገድ መቸገሯንም ገልጸዋል። ጡረተኞቹ የተፈቀደላቸውን የጡረታ አበል በየወሩ እየተከፈላቸው ባለበት ሁኔታ መንግስት ማስተካከያና ጭማሪ በማድረጉ ለእኛም ይፈቀድ በሚል ያቀረቡት ቅሬታ "ተቀባይነት የለውም፤ የሃይማኖት ተቋም እና መንግስት የተለያዩ ናቸው" የሚል ምላሽም ሰጥተዋል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ መንግስታዊ አሰራርን ከሃይማኖት ተቋም አሰራር ጋር ከህግና መመሪያ ውጪ በማቀላቀል ያቀረቡ መሆኑን በመግለጽ ጭማሪ እንዲደረግ የመወሰን ስልጣን ባለቤት የሆነው የቤተክርስቲያኗ ቋሚ ሲኖዲዮስ የካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ጉባኤ ቤተክርስቲያኗ በጀት የሌላት በመሆኑ ጥያቄያቸው ተቀባይነት የለውም ሲል ውሳኔ ማስተላለፉን አስረድተዋል። ይሁን እንጂ ቤተክርስቲያኗ በአሁኑ ሰዓት ያላት ገቢ እየተሻሸለ በመምጣቱ ከቅሬታ አቅራቢዎቹ ጋር በመነጋገር መፍትሄ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላት ገልፀዋል።