አካባቢያዊ ሰላምን በማስጠበቅ ሀገራዊ ክብርን ማስቀጠል ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን - ኢዜአ አማርኛ
አካባቢያዊ ሰላምን በማስጠበቅ ሀገራዊ ክብርን ማስቀጠል ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን
አሶሳ ጥቅምት 11/2014(ኢዜአ) አካባቢያዊ ሰላምን በማስጠበቅ ሀገራዊ ክብርን ማስቀጠል እንደሚገባ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን አስገነዘቡ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፀረ–ሽምቅ ፖሊስ አባላትን ዛሬ አስመርቋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደገለጹት ሀገርን እንደ ሀገር ለማስቀጠል አካባቢያዊ ሰላምን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው።
አካባቢያዊ ሰላምን በማረጋገጥ ሀገራዊ ክብርን ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በክልሉ ሰላምና የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ የጸጥታ መዋቅሩን የማጠናከር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር የፀጥታ ኃይሎች የማይተካ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ፌዴራል ፖሊስና የክልሉ ልዩ ኃይል መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡም በተደራጀ መልኩ አካባቢውን እንዲጠበቅ አሳስበዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱልአዚም መሐመድ በበኩላቸው "የክልሉ ፖሊስ ለውጡን ለማስቀጠል የህብረተሰቡን ደህንነት መጠበቅ ላይ ትኩረት አድርጓል" ብለዋል።
በአንዳንድ የክልሉ አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶችን ወደ ብሄር ለመቀየር የሚደረግ ጥረትን በዘላቂነት ለማስወገድ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ "በክልሉ የሚከናወነውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ ልማትን ማስፋፋትና ሰላምን ማስቀጠል የግድ ነው" ብለዋል።
"የሁሉም ክልሎች ልዩ ሃይሎች በጋራ እየከፈሉ ባለው መስዋእትነት ህወሃት በመተከል የፈፀመው ሴራ እየከሸፈ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የክልሉን ሰላም ወደ ቀደመ ሁኔታ ለመመለስ ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊው አስታውቀዋል።
ተመራቂዎች በሥልጠና ያገኙትን ዕውቀት በተግባር እንዲያውሉ አሳስበዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሱሆን አዲሱ የክልሉ ፖሊስ የደንብ ልብስና ዓርማ ይፋ ሆኗል።