ቀጥታ፡

የሀገር ህልውና የማስጠበቅ ዘመቻው በተሳካ ሁኔታ ይከናወናል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሀገር ህልውና የማስጠበቅ ዘመቻው በተሳካ ሁኔታ ይከናወናል ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር ድኤታ ማርታ ሉዊጂ ተናገሩ፡፡

በሶማሊያ ሰላም ማስከበር ላይ በሚገኘው ሴክተር 3 የአሚሶም እና ከአሚሶም ጥላ ስር ውጭ ያሉ ድጋፍ ሰጪ ሰራዊት አባላት ለህልውና ዘመቻ ለተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። 

የመከላከያ ሚኒስትር ድኤታ ማርታ ሉዊጂ በዚሁ ወቅት አሸባሪው ህወሃት የደቀነውን የህልውና አደጋ ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ በድል እንደሚመክቱት ተናግረዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላሟንና አንድነቷን ታረጋግጣለች ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ የምትታወቀው በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም በማስከበር መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ተልእኮ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡

በሶማሊያ ሰላም በማሰከበር ላይ ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝም  ነው ያነሱት፡፡

በሰላም ማስከበር ላይ የሚገኙ የሰራዊቱ አባላት ላደረጉት ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሱማሊያ ሰላም ማስከበር ሴክተር 3 ዘመቻ ኃላፊ የሆኑት ኮሎኔል ጋተው የጠዳ በበኩላቸው ሰራዊቱ ድጋፉን ያደረገው ለሀገሩ ህልውና መጠበቅ ዘብ ለቆመው የመከላከያ ሰራዊት ያለውን አጋርነት ለመግለጽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሁሉም ነገር የሚከናወነው ሀገር ሲኖር ብቻ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ ተልዕኮ በተሰጠን ቦታ ሁሉ አገራችንንና ህዝባችን ለማገለገል ሁሌም ቁርጠኛ ነን ብለዋል፡፡ማ

በሶማሊያ ሰላም በማስከበር ላይ የተሰማራው ሰራዊት በቀጣይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት፡፡

በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር የተሰማራው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተልዕኮውን በብቃት በመፈጸም ሶማሊያ አሁን ላገኘችው አንጻራዊ ሰላም ጉልህ ሚና አበርክቷል፤ እያበረከተም ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም