የምግብ ሉዓላዊነት ኢትዮጵያ ራሷን ከተረጂነት የምታላቅቅበት ብቸኛ አማራጭ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ሉዓላዊነት ኢትዮጵያ ራሷን ከተረጂነት የምታላቅቅበት ብቸኛ አማራጭ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ከተረጂነትና ከተመጽዋችነት ለማላቀቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ዘርፍ ተዋናዮች ገለጹ።
የዘርፉ ተዋናዮች የአገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህል መዳበር እንዳለበትም ተናግረዋል።
የምግብ ሉዓላዊነት የራስን ምግብ በራስ አቅም ማምረት መቻል ማለት ሲሆን፤ ኢትዮጵያም 74 ሚሊዮን ሄክታር የሚታረስ መሬት እንዳላት መረጃዎች ያመላክታሉ።
እንደ ግብርና ሚኒስቴር መረጃ በኢትዮጵያ ከ1990 እስከ 2000 ዓ.ም ይታረስ የነበረው መሬት 9 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር የነበረ ሲሆን፤ ይህ አሃዝ ከ2000 እስከ 2012 ዓ.ም ወደ 12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር አድጓል።
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየውም ከ36 በመቶ በላይ አነስተኛ እርሻ ያላቸው አርሶ አደሮች ከ0 ነጥብ 5 ሄክታር በታች መሬት እያረሱ ይገኛል።
ከ60 በመቶ በላይ አነስተኛ እርሻ ያላቸው አርሶ አደሮች ከአንድ ሄክታር መሬት በታች የሚያርሱ ሲሆን፤ ከ10 ሄክታር መሬት በላይ ያላቸው በቁጥር 14 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች ናቸው።
የስራ ፈጠራ አሰልጣኝ የሆኑት ዶክተር ወረታው በዛብህ ለኢዜአ እንደተናገሩት
ኢትዮጵያ ሌሎች ያልተሰጣቸውን ጸጋ ይዛ በድህነት ውስጥ መሆኗ እና ዜጎቿ ለችግር መጋለጣቸው ሊያስቆጨን ይገባል ።
ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ አገራት ለስደት እየተዳረጉና እየተሰቃዩ ያሉትም አገሪቷ የተፈጥሮ ፀጋዎቿን ተጠቅማ ራሷን ማሳደግ ባለመቻሏ እንደሆነ ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ሀብት ይዛ በየቀበሌው የስራ አጥነት መታወቂያ የሚያወጣ ሰው እንዴት ሊበዛ ቻለ?" የሚለው ጉዳይ ሁሉም ራሱን ሊጠይቅ የሚገባው ጥያቄ ነው ሲሉም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ሁሉም የተሰጣት አገር ናት፤ ይህን ጸጋ ወደ ዕድል በመቀየር ችግሮቿን መቋቋም ይቻላል ብለዋል።
ያደጉ አገራት በኢትዮጵያ ትከሻ ላይ መዳፋቸውን በመጫን ማደግ የለብሽም እያሏት ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ኢትዮጵያ መመንጠቅ አለባት፤ ለዚህም ጸጋዋን በአግባቡ መጠቀም ይገባታል ሲሉ ተናግረዋል።
ከተረጂነትና ተመጽዋችነት ለመላቀቅ በቁርጠኝነት መነሳትና የስራ ፈጠራ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በየተሰማሩበት የሙያ መስክ ተግቶ መስራትና ጠንካራ የስራ ባህልን መፍጠር እንደሚያስፈልግም እንዲሁ።
በየተሰማሩበት የሙያ መስክ ተግቶ መስራትና ጠንካራ የስራ ባህልን መፍጠር እንደሚያስፈልግም እንዲሁ።
ዶክተር አዲስ ከበደ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያላትን የእርሻ መሬት አሟጣ በመጠቀም፣ የመስኖ ልማት በማጠናከር፤ የግብርና ምርታማነቷን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም የአርሶ አደሩን የመሬት ይዞታ ባለቤትነት የሚያረጋግጡ ስራዎች መከናወን አለባቸው ብለዋል።
ለአምራቹ ዘርፍ መንግስት የማበረታቻ ድጋፎችን በማድረግ የምርት ማሳደግ ስራዎችን ማከናወን፤ የምርት አቅርቦትን በማሳደግም ገበያውን ማረጋጋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ወጣት የተማረ አወቀ የዱናሚስ ማህበራዊ ስራ ፈጣሪ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ኢትዮጵያዊያን የአገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀምን ባህል በማድረግ አገር ወዳድነታቸውን በተግባር ማስመስከር እንደሚጠበቅባቸውም ነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ተዋናዮቹ የተናገሩት።
ኢትዮጵያ ራሷን ከተረጂነት ለማላቀቅ ብቸኛው መንገድ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ መሆኑንና በዚህም ላይ አበክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ናቸው።
የዜጎችን የምግብ ፍላጎት በራስ የምርት አቅም የመሙላት ስራ በመከወን ከውጭ አገራት ምርት ጠባቂነት መላቀቅ ይገባልም ብለዋል።
በግብርና ዘርፍ በበሬ እያረስን ከዓለም መወዳደር አንችልም ያሉት የኢኮኖሚ ዘርፍ ባለድርሻ አካላቱ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና ግብዓቶችን መጠቀምና በራስ አቅም ማምረት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመንግስት በኩል ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ በመልሶ ማቋቋም እቅዱ አንድም የእርሻ መሬት ጦሙን እንዳያደርግ በሚለው አስተሳሰብ ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩም ተመልክቷል።
ኢትዮጵያ ያለችበትን ችግር እንድትሻገር ዜጎች በጋራ መቆም እና እርስ በእርስ መረዳዳትና መተጋገዝ እንደሚገባቸውም አክለዋል።