በነቀምቴ ከተማ የጽዳት ዘመቻ ተካሄደ

60
ነቀምቴ ነሀሴ 12/2010 በነቀምቴ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የጽዳት ዘመቻ ትናንት ተካሄደ። በከተማዋ በሁሉም ቀበሌዎች በተካሄደው የጽዳት ዘመቻ ላይ አባጋዳዎችን ጨምሮ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የፀጥታ አስከባሪ አካላት፣ ወጣቶችና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል። የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር የጽዳትና አረንጓዴ ልማት የስራ ሂደት መሪ አቶ ደሳለኝ ቦገንጃ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የጽዳት ዘመቻው ዓላማ ከተማዋን ጽዱና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ በመካሄድ ላይ ላለው ጥረት የከተማውን ህብረተሰብ ተሳትፎ ለማሳደግ ነው፡፡ ከተማዋን በሁሉም ወገን ተመራጭና ሳቢ ለማድረግ የከተማ ጽዳት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው የዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። በጽዳት ዘመቻው ላይ ከተሳተፉት መካከል የቄሶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ግርማ ታዬ በሰጡት አስተያየት የከተማ ንጽህና መጠበቅ ለአከባቢው ህብረተሰብ ጤንነትና ኑሮ  ወሳኝ በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ የ04 ቀበሌ ነዋሪው አቶ አካሉ ተስፋዬ በበኩላቸው ‘‘የከተማዋ ጽዳት መጠበቁ በተለይ በክረምት ወቅት ከወባና ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎች እንድንጠበቅ የሚያበረክተው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ለዘመቻው በፍላጎት ወጥቻለሁ'' ብለዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዘመቻ የአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ዘውትር ሊካሄድ ይገባል ያሉት ደግሞ የ03 ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ አሰለፈች ታደሰ ናቸው። የአከባቢ ጽዳትን ነዋሪው በባለቤትነት በመያዝ በተለይ ቆሻሻን ጨለማን ተገን በማድረግ ከመጣል ሊቆጠብ እንደሚገባው አመልክተዋል። በዘመቻው በቆሻሻ ምክንያት የተዘጉ የጎርፍ መሄጃ ቱቦዎችና የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች የማጽዳት ስራ መከናወኑ ታውቋል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም