ቀጥታ፡

ዘ ቴሌግራፍ በኢትዮጵያ ጉዳይ በተዛቡ እና በተሳሳቱ መረጃዎቹ አንባቢውን ማደናገሩን ቀጥሎበታል

ጥቅምት 10/2014 (ኢዜአ) ዘ ቴሌግራፍ የተሰኘው የእንግሊዙ ሚዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተናገሩትን ንግግር አዛብቶ በመልቀቅ ሙያውን የማይመጥን ስራ መስራቱን ቀጥሏል ሲል የኢትዮጵያ ወቅታዊ መረጃ ማጣሪያ አስታውቋል።

ዘ ቴሌግራፍ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ያደረጉትን ንግግር በማሳሳት እንዲሁም ከአውድ ውጪ ትርጉም ሰጥቶታል ብሏል።

ዘ ቴሌግራፍ በበሬ ወለደ ዘገባው "የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር የእርዳታ ምግብ ወደ ሀገራቸው እንዳይገባ አስቆማለሁ ብለው ዝተዋል" በሚል የተሳሳተ ዘገባውን ለአንባቢዎቹ አስነብቧል።

የኢትዮጵያ ወቅታዊ መረጃ ማጣሪያ ዘ ቴሌግራፍ ባወጣው ዘገባ ዙሪያ ባደረገው ጥልቅ ማጣራት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በአማርኛ ያደረጉት ንግግር ሌላ ሆኖ አግኝቶታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማርኛ የተናገሩት ንግግር "በግብርናው ላይ በደንብ ሰርተን ስንዴ ከውጭ እንዳይገባ በማድረግ 70 በመቶ የኢትዮጵያ የስንዴ ችግር መቅረፍ እንችላለን" የሚል ትርጉም እንዳለው አስረድቷል።

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስንዴ ከውጭ እንዳይገባ በሚል የተናገሩት እራስን በምግብ ከመቻል እና የውጭ ጥገኝነትን ከመቀነስ አንጻር እንደሆነ ሊሰመርበት እንደሚገባ ተመልክቷል።

ወቅታዊ መረጃ አያይዞም ዘ ቴሌግራፍ መረጃውን የመተርጎም ፈተና ከገጠመው እርዳታ መጠየቅ እንጂ የተሳሳተ እና የተዛባ መረጃን ለአንባቢዎቹ ማድረስ አይገባውም ብሏል።

በመሆኑም ሚዲያው ኢትዮጵያ ላይ የሰራው ዘገባ ከአውድ ከመውጣት ወይም ከማሳሳት ባለፈ የጋዜጠኝነት ሙያን ባከበረ እና እውነትን መሰረተ ያደረጉ ዘገባዎችን ለመስራት እራሱን እንደገና ቆም ብሎ ማየት እንደሚገባውም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም