ደሴ ከተማ መደበኛ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዋን እያካሄደች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ደሴ ከተማ መደበኛ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዋን እያካሄደች ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 10/2014 (ኢዜአ) የደሴ ከተማ የአሸባሪው ህወሃት የጥፋት ዓይን እንዳረፈባት ሳይሆን ሰላማዊ የሆነውን መደበኛ የማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዋን በማካሄድ ላይ ትገኛለች።
በአሸባሪው ህወሃት እና ተላላኪዎቹ የሚዘወሩ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና ማህበራዊ ትስስር ዘዴዎች "ደሴ፣ ሃይቅና ውጫሌ ከተሞችን ተቆጣጥረናል" በማለት የተለመደ ሀሰተኛ የማደናገሪያ ፕሮፖጋንዳቸውን ሲያስተጋቡ ይሰማል።
ይህም አሸባሪው ህወሃት ከተሞቹን ለማውደም፣ ለመዝረፍና ለማጎሳቆል ምን ያህል ጽኑ መሻት እንዳለው በግልጽ ያሳያል።
ይህ ሕዝቡን በሀሰተኛ ወሬ በማደናገርና ትርምስ በመፍጠር ወደ ከተሞቹ ዘልቆ ለመግባትና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ለመፈጸም አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ያሳያል።
ሆኖም የደሴ ነዋሪዎች፣ ወጣቶችና ጎልማሶች አካባቢያቸውን በንቃት ለመጠበቅ በወሰዱት አቋም የጠላት ሀሰተኛ ወሬ መክኗል።
ቀደም ሲል አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎችን በወረራ በመያዝ በርካታ ንጹሃንንና የሃይማኖት አባቶችን ገድሏል፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ ከብቶች በጥይት ደብድቦ ገድሏል፣ ንብረት አውድሟል።
"ከአማራ ጋር ሂሳብ አወራርዳለሁ" በሚል በጀመረው ጥቃት በርካታ ዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ፈጽሟል፤ እየፈጸመም ይገኛል።
የመንግስትና ግል ተቋማትን ንብረቶች በመዝረፍና በማውደም በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች ባዶ የሚያስቀር ዘራፊ ቡድን መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።
አሻባሪው ህወሃት በተከታታይ በሚፈጽማቸው ጥቃቶች ህዝብ ለከፋ አደጋ እያጋለጠ መሆኑን ሁሉም ተገንዝቦታል።
የደሴ ህዝብ ይህን ከአካባቢ የሚያፈናቅልና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የሚፈጽምን የጠላት ሃይል በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ መመከት ወሳኝ አድርጎ ይዞታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተሮች በደሴ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ባደረጉት ምልከታ የአሸባሪው ህወሃት ጽንፈኛ ታጣቂ በየመገናኛ ብዙሃኑ የሚነዛው ወሬ ሀሰተኛ መሆኑን በተጨባጭ አረጋግጧል።
በምልከታውም የደሴ ከተማ ነዋሪዎች መደበኛ ሰላማዊ የእለት ተዕለት እንቅስቃሲያቸውን በማካሄድ ላይ እንደሚገኙም ለማረጋገጥ ችሏል።
በከተማ የሚገኙ በርካታ የንግድ ድርጅቶች፣ ምግብ ቤቶች፣ ሱቆች፣ ታክሲዎች፣ የመንግስት ተቋማት እና ሌሎች ማህበራዊ ግልጋሎት ሰጪ ተቋማትም መደበኛ ስራዎቻቸውን በማካሄድ ተገልጋዮቻቸውን በማስተናገድ ላይ ይገኛሉ።
የከተማዋ ወጣቶችም የከተማቸውን ሰላምና ደህንነት ለማስቀጠል ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ቅንጅት ፈጥረው ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ በቁርጠኝነት እየሰሩ እንደሚገኝ ለመታዘብ ችለዋል።
ይህም መንግስት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወጣት፣ ሴት፣ ጎልማሳ ሳይል ከጸጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ ጠላትን እንዲመክት ላደረገው ጥሪ ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠ ነው።