የልማት ዕቅዶቻችንን ለማሳካት ገቢ አሰባሰብ ላይ ትኩረት ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
የልማት ዕቅዶቻችንን ለማሳካት ገቢ አሰባሰብ ላይ ትኩረት ይደረጋል
እንጅባራ ፤ ጥቅምት 9/2014 (ኢዜአ) በሁሉም መስክ የተያዙ የልማት እቅዶችን በስኬት ለማጠናቀቅና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ገቢ አሰባሰብ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የአዊ ብሔረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኛው ተናገሩ።
የአዊ ብሔረሰብ ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ለ2014 የስራ ዘመን የልማት ስራዎች ማስፈፀሚያ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጽድቋል።
በምክር ቤቱ ጉባኤ የተሾሙት ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት፤ ካለፉት ዓመታት ልምዶች በመነሳት በብሔረሰብ አስተዳደሩ የገቢ አማራጮችን በመለየት በትኩረት ይሰራል።
ዞኑ የውስጥ ገቢውን ማሣደግ የሚያስችል አቅም እንዳለው ገልጸው፤ የልማት ጉድለቶችን ለማሟላት የገቢ አቅምን ማሳደግ አማራጭ የለውም ብለዋል።
የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰብልና እንስሳት ልማት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ የበጋ መስኖን ጭምር በመጠቀም በዘመናዊ አስተራረስ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የዋጋ ንረትን በመፍጠር የኑሮ ውድነት በሚያባብሱ ህገወጦች ላይም የተቀናጀ ክትትል በማድረግ እርምጃ እንደሚወድ አስታውቀዋል።
የዞኑ ህዝብም ከልማት ሥራው በተጓዳኝ በግንባር ለተሰለፈው የፀጥታ ኃይል ሲያደርግ የነበረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ እስከመጨረሻው አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የዞኑ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መዓዛ አጉማሴ በበኩላቸው፤ የፀደቀው በጀት የአስር ዓመቱን መሪ ዕቅድንና ሁሉን አካታች ኢኮኖሚ ዕድገትን ማረጋገጥን ላይ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የልማት ስራዎች በድህነትና ሥራ አጥነትን መቀነስ እንዲሁም የወረዳዎችን የበጀት ድልድል መሠረትን በማየት እንደተዘጋጀ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
ከዘመኑ በጀት ውስጥ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚበልጠው በክልሉ የሚሸፈን፤ ቀሪው ደግሞ ከወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር አገልግሎቶች የሚሰበሰብ ነው ብለዋል።
በጀቱ በለፈው የስራ ዘመን ጥቅም ላይ ከዋለው ጋር ሲነጻጸርም በ19 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመላክተዋል።
የምክር ቤቱ ጉባኤ ዋና አፈ ጉባኤና የዞኑን ዋና አስተዳዳሪ ጨምሮ ሌሎች የካቢኔ አባላትን ሹመት እንዲሁም የቀረበውን በጀት መርምሮ በማፅደቅ መረሃ ግብሩን አጠናቋል።