"ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ሁላችንም ዘብ እንቁም" - ኢዜአ አማርኛ
"ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ሁላችንም ዘብ እንቁም"
አዲስ አበባ ጥቅምት 9/2014(ኢዜአ) "ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ሁላችንም ዘብ ልንቆም ይገባል" ሲሉ የምስራቅ ሐረርጌ እና ሱማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መቃሪዮስ ተናገሩ።
ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መቃሪዮስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ "ኢትዮጵያዊያን ከየትኛውም ጊዜ በላይ አገራቸውን መጠበቅ፣ ለሰላማቸው ዘብ መሆን፣ ለአንድነት በጋራ መቆም ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።
አገር ሰላም ካልሆነች የዜጎች መኖር አደጋ ላይ ስለሚወድቅ "ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ዘብ ልንቆም ይገባል" ነው ያሉት።
ከግጭት ሞትና ውድመት እንጂ ምንም አይነት ትርፍ አይገኝበትም እና ሁላችንም የአገራችን መድህን አንሁን ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
አሁን ላይ እያንዳንዱ ዜጋ በልማትም ይሁን በሰላም ግንባታ መንግስትን ልንደግፈው ይግባል ነው ያሉት።
"ኢትዮጵያ ምንም አይነት ፈተና ቢያጋጥማት ትሻገረዋለች፤ ወደ ፊትም ትቀጥላለች" ብለዋል ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መቃሪዮስ።
የኢትዮጵያ ጉዳይ የሁላችንም በመሆኑ ለአገራችን ሰላም፣ ልማትና አብሮነት እንስራ ያሉት ደግሞ ከአሜሪካ ማሕበረ ካህነት መላዕከ ስበሀት አብይ ስልጣን ናቸው።
በመሆኑም ልዩነትን ወደ ጎን በመተውና አንድነትን በማጠናከር በየቦታው የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቀነስ በቅንጅት መስራት አማራጭ የሌለው የሁላችንም የቤት ስራ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን የውጭ ጫና ለመቋቋም ሁሉም በተሰማራበት ሙያ ስኬታማ በመሆን አገሩን አሸናፊ ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን ተጨማጭ አውነታ ለመላው ዓለም ለማስረዳት በየትኛውም የመረጃ አማራጭ ተደራሽ በማድረግ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግም ይጠይቃል ብለዋል።
በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የማሕበረ ካህናት 11 ሊቃነ ጳጳሳት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመወያየት በነጩ ቤተ- መንግስት ተገኝተው የአሜሪካን ባለስልጣናት ለማነጋገር መሞከራቸውን ጠቅሰው በቀጣይም ጥረቱ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።