ቀጥታ፡

ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ ሶስተኛ ጨዋታውን ነገ ያካሂዳል

አዲስ አበባ ነሀሴ12/2010 ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የማጣሪያ እግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሶስተኛ ጨዋታውን ነገ ያካሂዳል። በ2011 ዓ.ም በታንዛኒያ በሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር የሴካፋ ዞንን ወክሎ የሚሳተፈውን ቡድን ለመለየት ከነሐሴ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በታኒዛንያ የማጣሪያ ጨዋታ እየተካሄደ ይገኛል። የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ነገ ከቀኑ ስምንት ሰዓት በቻማዚ ስታዲየም ከደቡብ ሱዳን ጋር ይጫወታል። ብሔራዊ ቡድኑ ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች የኡጋንዳን ብሔራዊ ቡድን 1 ለ 0 ፣ የጅቡቲ አቻውን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፉ የሚታወስ ነው። በዚህም መሰረት በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ስድስት ነጥቦችን በመሰብሰብ በአምስት የግብ ክፍያ በምድብ አንድ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ነገ በምድብ አንድ በሚደረግ ሌላ ጨዋታ ኬንያ ከኡጋንዳ ከቀኑ 11 ሰዓት በቻማዚ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ትናንት በምድብ አንድ በተደረጉ ጨዋታዎች ኬንያ ጅቡቲን 9 ለ 0 ፣ ኡጋንዳ ደቡብ ሱዳንን 6 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ችለዋል። በዚሁ መሰረት ምድብ አንድን ኬንያ በስድስት ነጥብና 13 የግብ ክፍያ በአንደኝነት ስትመራ ኢትዮጵያ በስድስት ነጥብና በአምስት የግብ ክፍያ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። ኡጋንዳ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ ይዛ በአራት የግብ ክፍያ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ትናንት የተመዘገበውን ውጤት ተከትሎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ የሚደረገው ፉክክር አጓጊ የሆነ ሲሆን በቀጣይ የሚደረጉ ጨዋታዎች በጣም ተጠባቂ ናቸው። በምድብ ሁለት የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር የሴካፋ ዞን ውድድር አስተናጋጅ የሆነችው ታንዛኒያና ሩዋንዳ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል። የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ማጣሪያ ውድድር እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል። የማጣሪያ ውድድሩ በሰባት ዞን ተከፋፍሎ የሚካሄድ ሲሆን አሸናፊ የሚሆኑት ሰባት ብሔራዊ ቡድኖች በአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም