ቀጥታ፡

አሸባሪው የህወሃት ቡድን “በተኩላ ለቅሶው” አሁንም የዓለም ማህብረሰብን ለማሳሳት እየሞከረ ነው

ጥቅምት 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪውና አጭበርባሪው የህወሃት ቡድን በተለመደው የተኩላ ለቅሶው ድርጊቱ እንዳይታወቅበት “እየተጠቃን ነው፤ ድረሱልን” በማለት አሁንም የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ለማሳሳት እየጣረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ቡድኑ ከሰሞኑ በውጫሌና ጭፍራ አካባቢዎች ላይ በፈጸመው የከባድ መሳሪያ ጥቃት ከ30 በላይ ንጹሃን ዜጎች መግደሉንም ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ተግባራዊ ካደረገ በኋላ አሸባሪው ህወሃት በአጎራባች አማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ ጥቃቶችን በመፈጸም በዜጎች ላይ ከፍተኛ አካላዊና ቁሳዊ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

አሸባሪው ህወሃት እያደረሰ ያለው ጭፍጨፋና ግድያ እንዳይታወቅበት ለመሸፋፈን የተለመደውን "የተኩላ ጩሄት ቀጥሎበታል" ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው ይህ እኩይ ተግባሩ እንዳይታወቅበት በቅርቡ በተኩላ ለቅሶው ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ “እየተጠቃን ነው፤ ድረሱልን” በማለት የለመደውን የማሳሳት ተግባሩ ቀጥሎበታል ብሏል።አሸባሪው ቡድን ከሰሞኑም በውጫሌና ጭፍራ አካባቢዎች ላይ በፈጸመው የከባድ መሳሪያ ጥቃት ከ30 በላይ ንጹሃንን በመግደል በርካቶችን ከቤት ንብረታቸው ማፈናቀሉም ተጠቅሷል።

የሽብር ቡድኑ በዚህ ተግባሩ በመቀጠሉ ለመሰብሰብ የደረሱ ሰብሎችን በመዝረፍ ወደ ትግራይ ክልል በመጫን፤ መውሰድ ያልቻለውን ደግሞ እያወደመ እንደሚገኝ መግለጫው አስታውቋል።

የአሸባሪው ህወሃት ዘግናኝ ጭካኔን ለማውገዝ የዓለም መንግስታት በመዳዳቱ መንግስት ማዘኑን ገልጾ፤ “በጉዳታችን ላይ ጨው ለመጨመር” የአሜሪካና አጋሮቿ ከፍተኛ ሚኒስትሮች ስብሰባን ተከትሎ በችግሩ ላይ የህወሃት ደጋፊ የሚመስለው የአውሮፓ ፓርላማ ያወጣው መግለጫ ፍጹም የተሳሳተ ነው ብሏል ሚኒስቴሩ በመግለጫው።

በተደጋጋሚ እንደሚገለጸው አሸባሪው ለትግራይ ክልል የሚላኩ ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ለራሱ ዓላማ ከማዋሉም በላይ በክልሉ መብራትና ሌሎች አገልገሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ ለማስጀመር የተሰማሩ በርካታ የተቋማቱ ሰራተኞችን እየገደለ እንደሚገኝ መግለጫው አመላክቷል።

አሁንም ቢሆን ሰራተኞች ለህይወታቸው ዋስትና ሳይኖራቸው በትግራይ ውስጥ እንዲሰሩ ማስገደድ አዳጋች እንደሚያደርገው ገልጾ፤ ይህ እኩይ ድርጊት በክልሉ እየተጸባረቀ ያልተገደበ እርዳታ ለማድረስ አዳጋች እንደሚያደርገው መንግስት አስታውቋል።

በመሆኑም አሸባሪውና አጭበርባሪው የህወሃት ቡድን የሚያወጣቸው መግለጫዎች የራሱ ዕኩይ ተግባር እንዳይታወቅበት ነው።በዚህም በሽብርተኛው ጩሄት ምዕራባውያን ሳይወናበድ ይልቁንስ በሰሜን ወሎ፣ በጎንደር በዋግ ህምራ እና በአፋር ክልሎች የዜጎችን ሲቃይ ሊመለከት እንደሚገባ መንግስት ጥሪውን አቅርቧል።የኢትዮጵያ መንግስት አሜሪካንና አጋሮቿ በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ሚዛናዊ ያልሆነ አያያዝን መልሰው እንዲያጤኑትም ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም