ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የመውሊድ በዓልን ምክንያት በማድረግ በካሊድ በጎ አድራጎት ፋውንዴሽን ማዕድ አጋሩ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የመውሊድ በዓልን ምክንያት በማድረግ በካሊድ በጎ አድራጎት ፋውንዴሽን ማዕድ አጋሩ
ጥቅምት 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ 1 ሺህ 496ኛውን የመውሊድ በዓልን ምክንያት በማድረግ የወንድም ካሊድ የበጎ አድራጎት ፋውንዴሽን ለሚረዳቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች ማዕድ አጋርተዋል።
በአዲስ አበባ በሚገኘው የወንድም ካሊድ የበጎ አድራጎት ፋውንዴሽን እየተካሄደ በሚገኘው መርሃ ግብር ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ እና ሌሎችም እንግዶች ታድመዋል።
ፕሬዚዳንቷ ከ100 በላይ ለሆኑ በፋውንዴሽኑ ለሚገኙ እና ከጎዳና ተነስተው በስልጠና ላይ ለሚገኙ ወገኖች በአካል ተገኝተው ማዕድ አጋርተዋል።
በተጨማሪም ፕሬዚዳንቷ ለሌሎች ከ100 በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ቤታቸው ወስደው የሚጠቀሙባቸው የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዓሉን ምክንያት ለፋውንዴሽኑ 20 በጎችን ድጋፍ ማድረጉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመርሃ ግብሩ ላይ ተናግረዋል።
ወንድም ካሊድ የበጎ አድራጎት ፋውንዴሽን በተቋቋመ በአንድ ዓመት ጊዜ ከ1 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ለቁም ነገር ማብቃቱም ተገልጿል።