እርስ በርስ በመዋደድ የአገራችንን አንድነት እናጠናክር - ኢዜአ አማርኛ
እርስ በርስ በመዋደድ የአገራችንን አንድነት እናጠናክር
ጥቅምት 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) እርስ በርስ በመዋደድ የአገርን አንድነት ማጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር እድሪስ ገለጹ።
1 ሺህ 496ኛው የነቢዩ መሐመድ የልደት በዓል (መውሊድ) በታላቁ አንዋር መስጊድ በመከበር ላይ ይገኛል።በዓሉ የነቢዩ መሐመድን በረከቶች በማስተዋልና መንገዳቸውን በማሰብ እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር እድሪስ እንደገለጹት፤ የመውሊድ በዓል የሚከበረው ለመብላት መጠጣት ብቻ ሳይሆን የነብዩ መሐመድ ስራዎችን ለማስታወስና ለመውሰድ ነው።
“ነብያችን የአንድነት፣ የሰላም፣ የእኩልነት፣ የእዝነት ነብይ ነበሩ” ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲው፤ ‘የነብያችንን ትምህርት ወስደን የአገራችንን አንድነት ማጠናከር አለብን” ብለዋል።
እርስ በርስ በመዋደድ የአገርን አንድነት ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበው፤ ለሌላቸው በማዘን ማካፈል እንደሚገባ ገልጸዋል።“እርስ በርሳችን እንተዛዘን፣ እንቀራረብ፣ እንመካከር፣ እንተባበር፣ እንዋደድ” ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀነአ ያደታ በበኩላቸው በዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነብዩ መሐመድ ያስተማሯቸውን የሰላም፣ የፍቅር፣ የመከባበርና የመልካም ስነምግባር እሴቶችን መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።እሴቶቹ ለየዕለት እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አሊ ሙሀመድ የመውሊድ በዓል አላህን በመፍራት፣ ታላላቆችን በማክበር፣ ለታናናሾች በማዘን እንዲሁም የተቸገሩትን በመርዳት መከበር እንዳለበት አስገንዝበዋል።