የብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
የብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 07/2014(ኢዜአ) የብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ሥርዓተ ቀብር በአዲስ አበባ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ከቄስ ወርቅነህ ትኩና ከወይዘሮ አንጓች አታሌ በቀድሞ ስያሜው ጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረ ታቦር አውራጃ በፋርጣ ወረዳ ልዩ ስሟ መገንታ ቁስቋም በተባለች ደብር ሐምሌ 12 ቀን 1916 ዓ.ም ተወለዱ።
ብጹዕነታቸው ገና በሕፃንነት ዕድሜያቸው ከአባታቸው ከቄስ ትኩ ፊደል ቆጥረው ንባብ ለይተው ዳዊት ከደገሙ በኋላ የቃል ትምህርት መቅሰም እንደቻሉ በሕይወት ታሪካቸው ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በቅድስት ሥላሴ ካቱድራል ቤተ ክርስቲያን በኃላፊነት በነበሩበት ወቅት ለቤተክርስቲያኗ ቀና ተግባራት አከናውነዋል።
ብፁዕነታቸውም ለስራ ፈጣን ትጉህ እንደነበሩ ያነሱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ ዘመናዊና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ስለማድረጋቸውም ገልጸዋል።
በተለያዩ አድባራትና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር የዜማ፣ የድጓ እና የቅኔ ትምህርታቸውን ስለመከታተላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሀፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በንባብ ባሰሙት የህይወት ታሪክ ገልጸዋል።
የምስጢራት ሁሉ መፍቻ የሆነው ቅኔን የመማር ፍላጎት ስለነበራቸው ቆማ ፋሲለደስ በመሄድ ከመርጌታ ዐምደ ብርሃን ሰዋሰዎ ግዕዝንና ቅኔንም ተምረዋል።
በጣና ሃይቅ በምትገኘው ክረስቶስ ሰምራ ገዳም በ1931 ዓ.ም ምንኩስናን ስለመቀበላቸውም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከጵጵስና እስከ ፓትሪያሪክ የደረሱ አባቶችን በትምህርት ታንፀው እንዲወጡ ማድረጋቸው ነው በህይወት ታሪካቸው ላይ የተጠቆመው።
በግሪክና ቱርክ በነገረ መለኮት (ቲኦሎጂ) ትምህርታቸውን የወሰዱ ሲሆን፤ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤትም ለአራት ዓመታት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
በግሪክ “ሐልኪ” በተሰኘ የቲዎሎጅ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ በ1949 ዓ.ም ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
በ1950 ዓ.ም የሰዋስው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ዳይሬክተርና መምህር በመሆንም አገልግለዋል።
በ1952 ዓ.ም የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ልዩ ካቢኔ ሲቋቋም የመንፈሳዊ ጉዳዮች መምሪያ ዳይሬክተር በመሆን ለንጉሠ ነገሥቱ የሚቀርቡ መንፈሳዊ ጉዳዮችን በኃላፊነት መርተዋል።
በመቀጠልም የመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት በመሆን እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ለ14 ዓመታት በማገልገል ሁለቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ መወጣታቸውን የህይወት ታሪካቸው ያመለክታል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በወቅቱ ላስመዘገቧቸው አመርቂ ውጤቶችም ከኢትዮጵያ መንግሥት 1ኛ ደረጃ የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ባለ አምበል፣ 1ኛ ደረጃ የዳግማዊ ምኒልክ የክብር ኮከብ ባለ አምበል፣ የቅድሥት ሥላሴ ኒሻን በኮማንደር ደረጃ ያለ ፕላኩ፣ የቅድሥት ሥላሴ ኒሻን የኮማንደር ደረጃ ከነ ፕላኩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ከውጭ አገራትም ከግሪክ መንግሥት፣ ከግሪክ ቤተ ክርስቲያን፣ ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን (በግሪክ) እና ከላዝሩስ ኒሻን ከኦስትርያ (ቪዬና) ከወርቅና ሌሎች ቁሳቁሶች የተሰሩ የክብር አልባሳትና ሌሎች እውቅናዎችን ተችሯቸዋል።
በደርግ መንግስትም ያለምንም ወንጀል ከሰኔ 1966 እስከ 1975 ዓ.ም ለስምንት ዓመታት ያህል በእስር ላይ መቆየታቸው ተወስቷል።
ወደ ሰሜን አሜሪካ ከሄዱ በኋላም በኒውዮርክ የጽዮን ቅድስት ማርያምን ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን በማቋቋም በማደራጀት ለእምነቱ ተከታዮች ሰፊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደቡብ ካሊፎርኒያና አላስካ ግዛቶች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም ነበሩ።
ብፁነታቸውም በህይወት ዘመናቸው ዜና ሕይወቱ ለቅዱስ ጳውሎስ፣ ስለ እግዚአብሔር መኖር፣ ትምህርተ አበ ነፍስ፣ ክብረ ድንግል፣ ድንግልናዊ ሕይወት፣ የእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት፣ እንጸልይ፣ ማኅበራዊ ኑሮ በኢትዮጵያ፣ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ትምህርት እንዲሁም ሌሎች 23 መጽኃፍትን በተለያዩ ቋንቋዎች ለተደራስያን ያበረከቱ ሲሆን፤ 11 ለህትመት የተዘጋጁ መጽኃፍትን አቅርበዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ባለፈው ዓመት ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም በስጋ ነፍስ ቢያርፉም፤ በኮቪድ-19 ምክንያት አገር ቤት መጥቶ ሳያርፍ በጊዜያዊነት በሰሜን አሜሪካ እንዲቆይ መደረጉ ይታወሳል።
ብፁዕነታቸው በተወለዱ በ97 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በክብር አርፈዋል።