ቀጥታ፡

እየተገነቡ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ትክክለኛ እድገትና ብልፅግና መምጣት የሚያመላክቱ ናቸው

አዲስ አበባ፣  ጥቅምት 07/2014(ኢዜአ) እየተገነቡ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ትክክለኛ እድገትና ብልፅግና መምጣት የሚያመላክቱ መሆኑን በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት አባላት በአዲስ አበባ የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።

የዳያስፖራ አባላቱ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክትን፣ የታላቁ ቤተ መንግስት መኪና ማቆሚያን፣ አብርሆት ላይብረሪን፣ የአድዋ ሙዚየም፣ እድሳት የተደረገለትን የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እና እንጦጦ ፓርክን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ዳያስፖራዎች የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ትክክለኛ እድገትና ብልፅግና እውን ማድረግ እንደሚቻል የሚያመላክቱ መሆኑን ገልጸዋል።

ከኖርዌይ የመጡት ወይዘሮ ኢትዮጵያ ዓለማየሁ፤ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ዘመናዊ  ቴክኖሎጂን ያካተቱና የአገሪቷን ቀጣይ እድገትና ለውጥ አመላካች ናቸው ብለዋል።

"በአዲስ አበባ የጎበኘኋቸውን ፕሮጀክቶች በእጅጉ አድንቄያለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።  

በለንደን የሚኖሩት ፋሪስ ሙሀመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በጫና ውስጥም ሆና እየገነባቻቸው ያሉ ፕሮጀክቶች የቀጣዩን ብሩህ ተስፋ የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል።

የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በተቀመጠላቸው ጊዜ፣ እቅድና ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆኑም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በአሜሪካ የሚኖሩት አቶ አለማየሁ አበበ፤ በኢትዮጵያ በተለይም በቅርብ አመታት የተከናወኑት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ሁላችንንም አስደስቶናል ብለዋል።

የዳያስፖራ አባላቱ በጎበኙት ሁሉ መደሰታቸውን ገልጸው ወደሚኖሩበት አካባቢ ሲመለሱ ስለ አገራቸው ለሌሎች ለማስረዳት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን መጎብኘትና የልማቱ ደጋፊ መሆን እንዳለባቸውም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የስራ አስፈጻሚ አባልና የልዑኩ አስተባባሪ አቶ አለባቸው ደሳለኝ ዳያስፖራው ለአገሩ  እድገት እያደረገ ያለው ሚና የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና የድርሻቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት አባላት ከጳጉሜ 3 ቀን 2013 ጀምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ጉብኝት በማድረግ ላይ ሲሆኑ ቀደም ሲል ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጎብኝተዋል።

ከዚህም በተጓዳኝ ደም በመለገስ፣ ችግኞችን በመንከባከብ እና ሌሎች ሰብአዊ ተግባራትንም እያከናወኑ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም