ቀጥታ፡

ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ዝግጁ ሆነዋል

ጥቅምት 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን እውነት፣ ለመልማት ያላትን ፍላጎትና ቁርጠኝነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውን ዲፕሎማቶች አስታወቁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚያደርገው የአሰራር ማሻሻያና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥልጠናዎች ለዲፕሎማቶች ባሳለፍነው ሳምንት ተሰጥቷል።ሥልጠናው ዲፕሎማቱና የመሥሪያ ቤቱ ባልደረቦች በጋራ በመሆን ተንቀሳቅሰው እንደ አገር የተጀመረውን የለውጥ ሥራዎችና ተቋማዊ ሪፎርሞች ግባቸውን እንዲመቱ ለማስቻል ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።

የሥልጠናው ይዘት በአገራዊና ተቋማዊ ለውጦች፣ በመደበኛና ዲጂታል ዲፕሎማሲ ዘርፎች እንዲሁም በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርገ መሆኑም ተመልክቷል።ሥልጠናውን የተከታተሉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ ፓርኮችና የተለያዩ ፕጀክቶችን ዛሬ በጎበኙበት ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በስኬት ጉዞዋ ውስጥ በርካታ ፈተናዎችን እያለፈች የመጣችው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በምዕራባዊያን በኩል የዲፕሎማሲ ጫና ገጥሟታል።የዲፕሎማሲ ጫናውን በድል ለመወጣት ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።ነው የገለጹት።

በዚህም ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ አገራት የሚንቀሳቀሱ ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን እውነት ለማሳወቅ ከምን ጊዜም በላይ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።በኢኮኖሚ፣ በሕዝብ ለህዝብ እና በዲጂታል የዲፕሎማሲ ዘርፎች ርብርብ የማድረግን አስፈላጊነት አመልክተው፤ ለዚህም በትክክለኛ መረጃ ላይ ተንተርሰው እንደሚሰሩ ነው የሚናገሩት።በአልጀርስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማት ይስሃቅ ሽመልስ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ጥቅም ማሳወቅ እንደሚገባ ገልጸው፤ "ኢትዮጵያ ያላትን እውነታን ማስረዳት ይኖርብናል" ብለዋል።

በኬንያ የናይሮቢ ሚሽን የዳያስፖራ ክፍል ሃላፊ አምባሳደር ዶክተር ደስታ ወልደዮሃንስ ዲፕሎማቱ ነቃን ወታደር ሆኖ የአገሩን እውነት በማስገንዘብ የሚመጣውን ጫና እንደሚመክት ገልጸዋል።

በባህሬን የኢፌዲሪ ቆንስላ ጽህፈት ቤት የዲያስፖራ ቆንስላ ጉዳዮች ሃላፊና ዲፕሎማት አልማዝ ገበያው በበኩላቸው ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል የሚሉት አባባል እንዳይደርስ መረጃ እንዳይዛባ ትክክለኛውን መረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

በሞስኮ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪና ከፍተኛ ዲፕሎማት አምባሳደር ቻም ኡጋላ "በአንድነት ስንቆም የሚመጣብንን ጠላት መመከት እንደምንችል ታሪካችን ያሳያል" ብለዋል።በስዊዘርላንድ ሔግ የኢፌዴሪ ቆንስላ ጽህፈት ቤት የዳያስፖራ ጉዳዮች ሃላፊ አምባሳደር ዶክተር ቦጋለ ቶሎሳ በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚነሱ ነገሮች የሚመከቱት በኢትዮጵያዊያን ጥንካሬ መሆኑን ገልጸዋል።

"ስለዚህ እኛም አሁን ስራችን የሀገራችንን ጥቅም ለማስጠበቅ በጋራ መረባረብ ነው'' ብለዋል።በአሁኑ ወቅት በርካታ የውጭ ሃይሎች በአገሪቷ ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረጉ በመሆኑ ይህንን መመከት የሚችል የዲፕሎማሲ አቅም መገንባት ያስፈልጋል።በተለይም በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ የሐሰት ዘገባዎች በተደራጀ የዲፕሎማሲ ዘመቻ መመከት እንደሚገባ ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።

አምባሳደሮቹና ዲፕሎማቶቹ የኢትዮጵያ እውነትና የመልማት ፍላጎትና ቁርጠኝነቷን የማሳወቅ ስራ ከመቼውም ጊዜ ለማከናወን ዝግጁ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም