ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር አፍሪካዊ በሆነ የሰላም አማራጭ እንዲፈታ ቁርጠኛ አቋም ያላት አገር ናት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር አፍሪካዊ በሆነ የሰላም አማራጭ እንዲፈታ ቁርጠኛ አቋም ያላት አገር ናት
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ኢትዮጵያ የአፍሪካን ችግር አፍሪካዊ በሆነ የሰላም አማራጭ እንዲፈታ ቁርጠኛ አቋም ያላት አገር ናት" ሲሉ የአልጄሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራ ተናገሩ፡፡
አልጄሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗንም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
አልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራ በ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ለመካፈል አዲስ አበባ ይገኛሉ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከስብሰባው ጎን ለጎን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይታቸው በሁለቱ አገራት ግንኙነትና በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸው ተገልጿል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ራምታኔ ላማምራ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ሁሌም ቢሆን የአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ በሆኑ የሰላም አማራጮች እንዲፈቱ ቁርጠኛ አቋም ያላት አገር ናት፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላም፣ መረጋጋትና ብልጽግና እንዲሰፍንም ጉልህ ሚና እያበረከተች ነው።
በኢትዮጵያ በህዝብ የተመረጠ አዲስ መንግስት በመመስረቱ ደስታቸውን ያጋሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ የመስራት ፍላጎት እንዳላት ነው በአጽንኦት የገለጹት።
ሁለቱ አገሮች በንግድ እንዲተሳሰሩም አልጄሪያ ፍላጎት አላት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ባደረጉት ውይይት የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በተመለከተ የዓረብ ሊግ ሚዛናዊና ትክክለኛ አቋም እንዲይዝ ለማድረግ አገራቸው እንደምትሰራ ይፋ አድርገዋል።
አልጄሪያ በቀጣዩ ወር የዓረብ ሊግ ሊቀ መንበርነትን ቦታ ትረከባለች።