በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት የሚያስችሉ አማራጮች አሉ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት የሚያስችሉ አማራጮች አሉ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 05/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት የሚያስችሉ አማራጮች እንዳሉ ማጤናቸውን የውጭ ኩባንያ ተወካዮች ተናገሩ።
ከ40 በላይ የተለያዩ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የተሳተፉበት አራተኛው የኢትዮጵያ የግብርና፣ ምግብና መጠጥ ማቀነባበርና የፕላስቲክ ህትመት የንግድ ትርኢት በአዲስ አበባ ተከፍቷል።
በንግድ ትርኢቱ ላይ የሩሲያ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ህንድ እና ቱርክ ኩባንያዎች እየተሳተፉ ነው።
በዚህም በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት የሚያስችሉ ሰፊ አማራጮች እንዳሉ ማጤናቸውን የውጭ ኩባንያ ተወካዮቹ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ባለሃብቶች፣ ለአገር ውስጥ አምራቾች፣ ላኪዎች፣ አስመጪ ድርጅቶችና ኩባንዎች የንግድ ትርኢቱ ጥሩ እድል ይፈጥራል ተብሏል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ዓለም አቀፍ አምራችና ላኪ ድርጅት ባለቤትና ተወካዮች የንግድ ትርኢቱ በኢትዮጵያ ያለውን የገበያ ሁኔታ በማየት ኢንቨስት ለማድረግ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።
የሞሃን ፒ.ኤል.ሲ ባለቤት ሞየሪ ኳተሪ፤ በኢትዮጵያ በርካታ ያልተነኩ እድሎች መኖራቸውን በመጠቆም በፋብሪካ ምርት ሂደት ላይ ለመሰማራት የሚያስችሉ ሰፊ አማራጮች እንዳሉ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ በዘይት ምርት ላይ ያለውን የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ለመሙላት የሚያስችል የኢንቨስትመንት ፍላጎት አለን ያሉት ደግሞ የጎ.ኤም ግሩፕ ኢንዲያን ኩባንያ የሽያጭና የማርኬቲንግ ኃላፊው አንኩር ቼትሮዳ ናቸው።
የሞሃን ፒ.ኤል.ሲ ባለቤት ሞየሪ ኳተሪ በበኩላቸው፤ የውጭ አገር ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡ አገሪቷ ያላትን የሰው ሃይልና ጥሬ እቃ በመጠቀም እሴት ጨምረው ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
በሩሲያ የማዕድን ውሃና ለስላሳ መጠጦች አምራች የኤል.ሲ.ኤም ኩባንያ ኃላፊዋ በማዕድን ውሃና በለስላሳ መጠጥ ዘርፎች ላይ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሞየሪ ኳተሪ ጨምረው እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የገበያ ችግር ባለመኖሩ እድሎችን በመጠቀም አትራፊ መሆን እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
የጀርመኑ የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች ላኪ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ሰባስቲያን ሙለር፤ ኩባንያቸው በእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች በኢትዮጵያ ያለውን ገበያ ለመጠቀም የቢዝነስ አጋሮችን እያፈላለጉ መሆኑን ገልጸዋል።
የንግድ ትርኢቱን 2 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ ይጠበቃል።