የአፍሪካ አገራት በየዓመቱ ለምግብ ግዢ 45 ቢሊዮን ዶላር ያወጣሉ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ አገራት በየዓመቱ ለምግብ ግዢ 45 ቢሊዮን ዶላር ያወጣሉ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5/2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ አገራት በየዓመቱ የምግብ ምርቶችን ከውጪ ለማስገባት 45 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጡ የአፍሪካ ሕብረት አስታወቀ።
አገራቱ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ዋነኛ ትኩረታቸው አድርገው እንዲሰሩ ጥሪ ቀርቧል።
39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የሕብረቱ የ'ግብርና ገጠር ልማት ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ ከባቢ አየር' ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ በአፍሪካ የምግብ ስርዓት ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
አፍሪካ 60 በመቶ የሚታረስ መሬት እያላት ከውጭ የግብርና ምርቶችን ለማስገባት በየዓመቱ 45 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደምታደርግ አምባሳደር ጆሴፋ ገልጸዋል።
ይህን በየዓመቱ የሚወጣ ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስ የአፍሪካ አገራት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችላቸውን ስራዎች ማከናወን እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ለግብርና የሚያወጡትን ዓመታዊ የገንዘብ መጠን ማሳደግ፣ እምቅ የግብርና ምርት ያለባቸውን አካባቢዎች በክላስተር በመለየት ምርታማነትን ለማሳደግ መስራትና ምርት የሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂ የመጠቀም አቅማቸውን ማጎልበት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
አርሶ አደሮች በተለይም ሴት አርሶ አደሮች ለግብርና ፋይናንስ የሚያስፈልጋቸውን የብድር አቅርቦት ማመቻቸት እንደሚገባም አመልክተዋል።
"በአፍሪካ 50 በመቶ የሚሆኑት አርሶ አደሮች ሴቶች ናቸው" ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ለሴቶች ድጋፍ ማድረግ በአፍሪካ የግብርና ምርማነትን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የአፍሪካ አገራት የዜጎቻቸውን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መሆኑን ጠቁመው፤ "በመገንዘብ ለጉዳዩ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይገባቸዋል" ነው ያሉት አምባሳደር ጆሴፋ።
የአፍሪካ ሕብረት ለአባል አገራቱ የግብርና ምርታማነታቸው እንዲያሳድጉ የገንዘብ፣ የቴክኒክና የፖሊሲ ማዕቀፍ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ትናንት ከተወያየባቸው ጉዳዮች መካከል እ.አ.አ በ2022 የአፍሪካ ሕብረት መሪ ሀሳብ "የተመጣጠነ ምግብና የምግብ ዋስትና" እንዲሆን በቀረበው ሀሳብ ላይ ውይይት ማድረጉን አስታውሰዋል።
ምክር ቤቱ ሀሳቡ ነገ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በበይነ መረብ በሚያደርጉት ሶስተኛው የአጋማሽ ዓመት የጥምር ውይይት ላይ እንደ አጀንዳ አድርጎ እንደሚያቀርብና በውይይቱ መሪ ሀሳቡን ያጸድቀዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል እ.አ.አ በፈረንሳይ በተካሄደው 21ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የበለጸጉ አገራት እያደጉ ላሉ አገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን እንዲቋቋሙ የ100 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ቢገቡም ገንዘቡን እየሰጡ እንዳልሆነ አምባሳደር ጆሴፋ ገልጸዋል።
የበለጸጉት አገራት በሚለቁት በካይ ጋዝ ዋንኛ ተጎጂ የሆኑት በማደግ ላይ ያሉ አገራት መሆናቸውን አመልክተው፤ አገራቱ የገቡትን ቃል አለመፈጸማቸው ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አመልክተዋል።
በመሆኑም ያደጉ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ የፋይናንስ ድጋፉን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሕዳር 2014 ዓ.ም በስኮትላንድ ግላስኮው በሚካሄደው 26ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ መሰጠት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የአፍሪካ አገራት በአፍሪካ ሕብረት በኩል በጉባኤው ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥና ድምጻቸው እንዲሰማ በጋራ አቋማቸውን ለማንጸባረቅ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።