ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር አራተኛ ጨዋታዎች ከቅዳሜ ጀምሮ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 ስምንት ቡድኖች የሚሳተፉበት የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር አራተኛ ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚካሄዱ ጨዋታዎች የሚጀምር ይሆናል። በዚሁ መሰረት ቅዳሜ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይጫወታሉ። በክልል ከተሞች ሃዋሳ ከተማ በሜዳው ከየካ ክፍለ ከተማ እንዲሁም አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ በተመሳሳይ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ.ም ባህርዳር ላይ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ከወልቂጤ ከተማ ከጠዋቱ ሶስት ላይ ይካሄዳል። የፌዴራል መንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን ያለፉትን ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ሳይጫወት በመቅረቱ ፎርፌ የተሰጠበት በመሆኑ በህጉ መሰረት "በሁለት ተከታታይ ጨዋታ ፎርፌ የተሰጠበት ቡድን ከውድድሩ ውጭ ይሆናል" ስለሚል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከሊጉ ተሰናብቷል። በዚህም ምክንያት አምስት ቡድኖች ይሳተፉበት የነበረው የኢትዮጵያ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ወደ አራት ዝቅ ያለ ሲሆን፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን እንዲሁም ጎንደር ከተማ የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው። በሌላ በኩል ሰባት ቡድኖች የሚካፈሉበት የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊ ቦል ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ከጠዋቱ 2 ሰአት ከ30 ደቂቃ አዲስ አበባ ፖሊስ ከፌደራል ማረሚያ ይጫወታሉ። በክልል ከተሞች ጣና ባህርዳር በሜዳው ከሙገር ሲሚንቶ ከጠዋቱ 2 ሰአት ከ30 ደቂቃ ሶዶ ላይ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ወላይታ ድቻ ከመከላከያ ከቀኑ 8 ሰአት ከ30 ደቂቃ ላይ የሚጫወቱ ይሆናል። የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊ ቦል ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር የፊታችን እሁድ ከረፋዱ 4 ሰአት ከ30 ደቂቃ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊ ቦል ፕሪሚየር ሊግ አራት ቡድኖች በመወዳደር ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም