ቀጥታ፡

ከአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ሁለተኛ ቀን ውሎ ምን ይጠበቃል?

 አዲስ አበባ ጥቅምት 5/2014 (ኢዜአ) ከአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ሁለተኛ ቀን ውሎ ምን ይጠበቃል?
39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ትናንት አዲስ አበባ ተጀምሯል።

በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ተወካዮች፣ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብና በአፍሪካ ሕብረት ስር የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ሃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በመክፈቻ ንግግራቸው የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት አገራት ዘርፈ ብዙ የትብብር ግንኙቶችን መፍጠር እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የአፍሪካ አገራት እርስ በእርስና ከሌሎች የውጭ አገራት አጋሮች ያለቸውን ግንኙነት የሚመሩበት የትብብር ስትራቴጂና ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን አመልክተዋል።

አፍሪካ በአሁኑ ሰዓት ብዙ ፈተናዎች ገጥመዋታል ያሉት ኮሚሽነሩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና ረሃብን ከችግሮቹ መካከል በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲሲ) እና የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት ያደረጉትን ጥረት አድንቀው ወረርሽኙ ያጋረጠውን ፈተና ለመቋቋም አሁን በትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል።

የአፍሪካ አገራት ረሃብን በመከላከል የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል ነው ያሉት ሊቀመንበሩ።

የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበርና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፍ ሉቱንዱላ ሕብረቱ ጠንካራ ለማድረግ ሁሉን አቀፍ የማሻሻያ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

እነዚህ ማሻሻያዎች በአጀንዳ 2063 የበለጸገች፣ አንድነቷን የጠበቀችና ሰላማዊ አፍሪካን ለመፍጠር ለተያዘው እቅድ የራሱ አበርክቶ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

አፍሪካ በዓለም መድረክ ያላትን ተሰማኒነትና ሃይል ለመጨመር ማሻሻያዎቹ ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በበይነ መረብ የሚካሄዱ የሕብረቱ ውይይቶች በአካል መካሄድ መጀመሩ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በስብሰባው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ በኢትዮጵያ በአካል ተገነኝተው የሚኒስትሮቹ ስብሰባ መካሄዱ አስደሳች መሆኑን መናገራቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኢትዮጵያ ባካሄደችው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ልዑኩን በመላክ ለነበረው የታዛቢነት ሚና ምስጋና እንዳቀረቡም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ የገጠማትን ወቅታዊ የሰላምና የደህንነት ችግር ለመፍታት እየሰራች መሆኑን አቶ ደመቀ መናገራቸውንም ነው አምባሳደር ዲና ያመለከቱት።

የአፍሪካ ሕብረት የምክር ቤቱ ስብሰባ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟቿን ያስጠበቁ ጉዳዮቿን የምታንጸባርቅበት እንደሚሆን ገልጸው "የኢትዮጵያ ችግር በአፍሪካ ድጋፍና አመራር ድጋፍ ይፈታል" ነው ያሉት ቃል አቀባዩ።

ከስብስባው ጎን ለጎን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ትናንት ከቤኒን አቻቸው ኦሬሊየን አግቦኖቺ ጋር ባደረጉት ውይይት ቤኒን በኢትዮጵያ ኤምባሲ ለመክፈት መዘጋጀቷን መግለጻቸውን ነው አምባሳደር ዲና የገለጹት።

ከአልጄሪያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

አቶ ደመቀ ከላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ብሩንዲ፣ አንጎላና ከሌሎች አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳይ ላይ ይመክራሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በትናንትናው እለት በተጀመረው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።

በመስከረም 2014 ዓ.ም የተካሄደው 42ኛው የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ ተወካይ ኮሚቴ ስብሰባና የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል የአፈጻጸም ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎበታል።

ምክር ቤቱ "የተመጣጠነ ምግብና የምግብ ዋስትና" የአፍሪካ ሕብረት እ.አ.አ የ2022 መሪ ሃሳብ ሆኖ እንዲሰየም በቀረበው የመነሻ ሃሳብ ላይም ተወያይቷል።

በተጨማሪም በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ስር ለሚገኙ ሁለት ዘርፎች የኮሚሽነሮች እንዲሁም የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት ምርጫም ተካሄዷል።

በተጨማሪም የሠብዓዊና የዜጎች መብቶች ኮሚሽንና የአፍሪካ ሕብረት የፀረ-ሙስና አማካሪ ቦርድ በተመሳሳይ የአራት አባላት ምርጫ ተካሄዱ ነበር።

የአፍሪካ ሕብረት የምርጫውን ውጤት እስካሁን ይፋ አላደረገም።

በተያያዘም በሕብረቱ ስር የሚገኙ የተለያዩ ኮሚሽኖች በስራ አፈጻጸማቸው ዙሪያ መግለጫዎችን ሰጥተዋል።

በ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጸሚ ምክር ቤት የመጨረሻ ቀን ውሎ የተለያዩ ጉዳዮችን ይመለከታል።

በምክር ቤቱ በስሩ የሚገኙ የተለያዩ ኮሚቴዎች፣ ንዑስ ኮሚቴዎች በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ አፍሪካውያን ያላቸው ተሳትፎ፣ የአጀንዳ 2063 አፈጻጸምና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚቀርቧቸውን ሪፖርቶችን ያዳምጣል ተብሎ ይጠበቃል።  

ምክር ቤቱ የአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ የአፍሪካ ሕብረት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማኀበረሰብ ተቋማትና በሕብረቱ ስር የሚገኙ ተቋማት ነገ በበይነ መረብ ለሚያደርጉት የሶስተኛው አጋማሽ ዓመት ለሚያደርጉት ጥምር ውይይት አጀንዳዎችን ተወያያቶ እንደሚያጸድቅ የአፍሪካ ሕብረት አስታውቋል።

የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች የቀረቡ የውሳኔ ሀሳቦችን እንደሚያጸድቅም ገልጿል።

እስራኤል በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም በአፍሪካ ሕብረት ባገኘችው የታዛቢነት ቦታ በተመለከተም ውይይት የሚካሄድ ሲሆን ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት በሚያቀርቧቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ይደረጋል ተብሏል።

በአፍሪካ ሕብረት ስር የሚገኙ የተለያዩ ኮሚሽኖች እያከናወኗቸው ባሏቸው ስራዎች መግለጫ እንደሚሰጡም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም