በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ የአፍሪካን ቀንድ የማተራመስ እሳቤ

3250

አሜሪካዊው የፖለቲካ ተንታኝና ጋዜጠኛ አንድሪው ኮርይብኮ ‘Analyzing the American Hybrid War on Ethiopia’በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቁት ትንታኔያቸው አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ባለ ብዙ መልክ አሊያም ቅይጥ ጦርነት እያካሄደች ስለመሆኗ ይናገራሉ። ነገሩ ተጨማሪ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም በሰብዓዊ ድጋፍ ሰበብ ሶሪያ ላይ የፈጸመችውን ድርጊት በሚመሰል መልኩ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች ነው ይላሉ።    

በትግራይ ክልል የተፈጠረው ቀውስ መንስኤው የሽብር ቡድኑ መሆኑን የሚናገሩት ጸሐፊው፤ የጀመረውም በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ በፈጸመው ጥቃት መሆኑን ያስረዳሉ። ይህንን እውነታ አሜሪካና አጋሮቿ በውል መገንዘብ የፈለጉ አይመስልም ሲሉም ይተቻሉ። ሁኔታውን በቅጡ መገንዘብ ያልፈለጉት አሜሪካና አጋሮቿ ማዕቀብ ለመጣል እያሴሩ መሆኑን ይገልጻሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግስት ከኤርትራና ከሶማሌያ ጋር ግንኙነቱን በማጠናከር በቀጠናው አካባቢ ተጽእኖ መፍጠር መጀመሩ ምእራባውያንን እንዳላሰደሰተ ጸሐፊው ይጠቁማሉ። ከዚህ በተጨማሪ በዋሽንግተንና በቤጂንግ መካከል ባለው ጂኦፖለቲካዊ ስበት በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ቀጣናዊ ሚዛን ጠብቀው ለመሄድ እያደረጉ ያለውን ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ የባይደንን አስተዳደር ምቾት የነሳው መሆኑን ያስረዳሉ። እናም ይህ እንዳልሆነ የተሰማት አሜሪካ አጋሮቿን አስተባብራ ኢትዮጵያ ላይ መልከ ብዙ ጫና መፍጠር የመፈለጓ ምክንያት ይኸው ነው ብለዋል አንድሪው ኮርይብኮ።

ከዚህ አኳያ አሸባሪው ህወሓት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የከፈተው ጦርነት አሜሪካ ከፈርጀ ብዙ ወይም ቅይጥ የጦርነት ገጽታዎቿ አንዱ ወደ ሆነው እርምጃ ለመግባት መልካም አጋጣሚ እንደተፈጠረላት ጸሐፊው ያስረዳሉ። አጋጣሚውን በመጠቀም ከተቻለ ህወሃትን ከመንግስት እኩል በማድረግ እንዲደራደርና ወደ ማእከላዊ ስልጣን እንዲመለስ ካልሆነም እጅግ የተለጠጠ የክልል ስልጣን እንዲኖረውና የፌደራል መንግስቱን እንዲገዳደር በማስቻል የማእከላዊ መንግስትን ጉልበት የማዳከም ስራዎች እየሰራች መሆኑን ያነሳሉ።

ለዚህ ደግሞ ከማዕቀብ አንስቶ እስከ ተለያዩ ጫናዎች መፍጠር የሚሉ ስልቶች ተቀምጠዋል። ተንታኙ እንደሚገልጹት የባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያን ከቻይና “ጂኦፖለቲካ ጨዋታ” በማውጣት የአሜሪካ ፍላጎቶችን የሚያራምድ መንግሥት መፍጠርን ይሻል። ይህን መቀበል ያልፈቀደው የኢትዮጵያ መንግሥት “የዘር ማጥፋት” ፈጽሟል የሚል ክስ እንዲቀርብበትና የማዕቀብ ሰለባ እንዲሆን ግፊት እየተደረገ መሆኑንም ያነሳሉ። እናም የአፍሪካ ቀንድን የማተራመስ ፍላጎት የማን ነው ለሚለው ጥያቄ የአሜሪካና አጋሮቿ አካሄድ ስለመሆኑ በትንሹ ምላሽ የሰጠ ነው ይላሉ ተንታኙ። በአሜሪካ የዜሮ ድምር አዲስ የቀዝቃዛ ጦርነት ጂኦፖሊቲካል ስሌት ምክንያት በአገራት የውስጥ ጣልቃ ገብነት እየተስተዋለ መሆኑን ተንታኙ አስምረውበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም