በአፍሪካ 11 አገሮች ሰላማዊና ተአማኒ ምርጫዎች አካሂደዋል

18

ጥቅምት 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአፍሪካ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ11 አገሮች የተካሄዱ ምርጫዎች ሰላማዊና ተአማኒ እንደነበሩ የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነሩ አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ገለጹ።

ኢትዮጵያም ያካሄደችው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን እንደታዘበውና ምርጫውም ሰላማዊና ተአማኒ እንደነበር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ምርጫ በተካሄደባቸው 11 አገሮች የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን ምርጫዎቹን መታዘቡን ጠቁመው፤ በምርጫው የተሳካና ሠላማዊ እንደነበር ገልጸዋል።  

አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ዛሬ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ፤ ኮሚሽኑ የአህጉሪቷን ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀዳሚነትም የኅብረቱን ሰላምና ደህንነት ተቋማት ማጠናከርና የአሰራር ሥርዓትን ይበልጥ ውጤማ የማድረግ እንቅስቃሴ ውስጥ በስፋት መገባቱን አመልክተዋል።

በሁለተኛ ደረጃ በአህጉሪቷ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥልቶችን ለማጠናከርና መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱንም ጠቁመዋል።

ለአብነትም የቅድመ ግጭት የጥንቃቄ ሥርዓትና ግጭትን የመከላከል ሥራ ማጠናከርና ከተከሰተም በኋላ ግጭቱ እንዳይስፋፋ መቆጠጣር ላይ ኅብረቱ ማተኮሩን ተናግረዋል።

ግጭትን በመቆጣጠር ማዕቀፍ ሥር ሰላምን ሊያመጡ የሚችሉ ውይይቶችና ድርድሮች በአፍሪካ እንዲስፋፉ እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በሦስተኛ ደረጃም በአህጉሪቷ በተለያዩ የግጭት ቀጣናዎች በኅብረቱ ሥር የተሰማሩ የሠላም አስከባሪ ሰራዊቶችን ለማጠናከር ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በአህጉሪቷ ለመልካም አስተዳደር እጦትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በመጨረሻም ሰላም ደኅንነት ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ከሚደግፉ አካላት ጋር ያለውን ትብብርና አጋርነት ማጠናከር ላይ ኮሚሽኑ ትኩረት ማድርጉን ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም