በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት ዜጎች መረባረብ አለባቸው

ጥቅምት 4/ 2014 (ኢዜአ) በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት ዜጎች ሁሉ እንዲሳተፉ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።
የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማህበራት ህብረት እና ማህበረ ካህናት ዘ ሰሜን አሜሪካ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ሲያደርጉት የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ የመዝጊያ መርሃ ግብር ዛሬ ተከናውኗል ።

በዚሁ ወቅት ሁለቱ አካላት በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ ዜጎች ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ  ከ3 ሺህ 500 ለሚልቁ ሰዎች የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጋቸው አስታውቀዋል።

የሃይማኖት አባቶቹ በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በተለያዩ የአማራና የአፋር ከተሞች ለተጠለሉ ዜጎች በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል ።

ቀደም ብሎ የተደረገው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው አሁንም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለተጎዱ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ሁሉም ህብረተሰብ በተለይ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የምስራቅ ሐረርጌ  እና ሱማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መቃሪዮስ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት ሁሉም ዜጋ መረባረብ አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

ከማኅበረ ካህናት አሜሪካ የመጡት መላዕከ ስብሀት አብይ ስልጣን፤ በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ በነበረው ግጭት ለተጎዱት ወገኖች ድጋፍ እንዳደረግን ሁሉ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያሉትን ለመርዳታ እየሰራን ነው ብለዋል።

የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማህበራት ህብረት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ንጉስ ለገሰ በበኩላቸው በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በህወሃት ወረራ ለተጎዱት ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቀሴዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም