ቀጥታ፡

የምርት ጥራትና ደረጃን ለማስጠበቅ ከመገናኛ ብዙሀን ጋር በቅንጅት ይሰራል-ኤጀንሲው

አዳማ ጥቅምት 4/2014 (ኢዜአ ) የምርት ጥራትና ደረጃን ለማስጠበቅ ከመገናኛ ብዙሀን ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጄንሲ አስታወቀ።

ኤጄንሲው ከመንግስትና ከግል መገናኛ ብዙሀን ለተወጣጡ ባለሙያዎች በምርት ጥራትና ደረጃ የህግ ማዕቀፎች፣ አሰራርና መመሪያዎች ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር ያዘጋጀው መድረክ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።

የኤጄንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦንሳ ባይሳ በወቅቱ እንደገለጹት የምርት ጥራትና ደረጃ በማስጠበቅ ጤናማና ጥራት ያለው የኢኮኖሚ መዋቅር ለመገንባት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ከመገናኛ ብዙሀን ተቋማት ጋር በቅንጅት ይሰራል ።

የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የምርት ጥራትና ደረጃ ለማስጠበቅ የወጡ ህጎች ፣ አሰራሮችና መመሪያዎች ዙሪያ ግንዛቤ ጨብጠው ለህብረተሰቡ እንዲያሰርጹና ዘርፉ በደረጃ አጠባበቅ ላይ የሚጠበቅበትን ሚና በአግባቡ እንዲወጣ ለማስቻል መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል ።   

አምራቾች የምርት ጥራትና ደረጃን ጠብቀው እንዲያመርቱ ለማስቻል የወጡ ህጎችና መመሪያዎች ተፈፃሚ መሆናቸውን በመከታተል ሂደት እንዲሁም ለህብረተሰቡ ተገቢና ወቅታዊ መረጃ ለማድረስ ከመገናኛ ብዙሀን ዘርፉ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አስታውቀዋል ።

በኢትዮጵያ ካሉ ከ11ሺህ በላይ ደረጃዎች 270 ዎቹ አስገዳጅ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ በኤጀንሲው የደረጃ ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ ይልማ መንግስቱ ናቸው።

የመገናኛ ብዙሀን ዘርፉ ደረጃ የወጣላቸው ምርቶች ጥራትና ተገቢውን ደረጃ አሟልቶተው እንዲመረቱ እገዛ ሊያደርግ ይገባል " ብለዋል ።

ምርትን ለህዝብ ለማሳወቅ ማስታወቂያ ከማስነገር ጀምሮ በጥራት፣ በደረጃና አገልግሎት ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ መገናኛ ብዙሀን ዘርፉ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠትና በመፈተሽ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል ።

"የምርት ጥራትና ደረጃ ለማስጠበቅ ለወጡ የህግና መመሪያ ተፈፃሚነት በቅንጅት እንሰራለን" ሲሉ ተናግረዋል።

"በተለይም ምግብና ምግብ ነክ ምርቶች በየትኛውም መመዘኛ ጥራትና ደረጃቸውን ጠብቀው መመረት አለባቸው" ያሉት ዳይሬክተሩ  በወጪና በገቢ ንግድ፣ በሰውና እንስሳት ጤንነትና ደህንነትን እንዲሁም  በአካባቢያዊ ደህንነት ዙሪያ የተቀመጡ  አስገዳጅ ደረጃዎች  በአግባቡ እንዲተገበሩ  ከመገናኛ ብዙሀን ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም