ቀርጫንሼ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በ1 ቢሊዮን ብር ወጪ የቡና ምርትን ለማዘመን እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቀርጫንሼ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በ1 ቢሊዮን ብር ወጪ የቡና ምርትን ለማዘመን እየሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 04/2014 (ኢዜአ) ቀርጫንሼ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የቡና ምርትን ለማዘመን እየሰራ ነው።
የማህበሩ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ እስራኤል ደገፋ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ማሕበሩ የቡና ልማት ዘርፉን ለማዘመን አንድ ቢሊዮን ብር መድቦ እየሰራ ነው።
ማሕበሩ ለቡና ልማት ዘርፍ ባዋለው ኢንቨስትመንትም ለ25 ሺህ 500 ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ቡና በአለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተቀባይነት እያደገ የመጣ በመሆኑ አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ለማሳደግ ከአመራረት ጀምሮ ክትትል ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በማጓጓዝ ሂደት የሚደርሰውን የቡና ምርት ብልሽት ለማስቀረት ከተመረተበት ቦታ ቀጥታ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት በጅማና ቡሌሆራ በተገነቡት ማእከላት የቡና ምርትን በቀጥታ ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ እንደሆኑም ጠቅሰዋል።
ማሕበሩ በቀጣዮቹ አምስት አመታት ከጊምቢ፣ ከሃረርና ከባሌሮቤ ቡናን ቀጥታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲቻል እየተሰራ መሆኑም አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ለውጡ ከመምጣቱ በፊት ነጋዴውና አርሶ አደሩ መገናኘት አይችልም ነበር ያሉት አቶ እስራኤል አሁን ላይ ችግሩ መፈታቱንም ጭምር ነው ያመለከቱት።
በዚህም ነጋዴው አርሶ አደሩን በቀጥታ የሚደግፍበትና አርሶ አደሩም ምርቱን ቀጥታ የሚያቀርብበት የአሰራር ስርአት መዘርጋቱን ተናግረዋል።
ማህበሩ ለአካባቢው አርሶ አደሮች የገንዘብ ድጎማ፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የቡና ችግኝ ድጋፍና ሌሎችም ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ማሕበሩ በ25 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ቡናን ያለ ጥላ በመስኖ ጠብታ ለማምረት እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ስራ አስኪያጁ በመንግስት በኩል የብድር አገልግሎት ማግኘት እንደሚሹ ተናግረዋል።
የአምራቹንና የንግዱን ዘርፍ ለመደገፍ ካስፈለገ የመንግስትና የአበዳሪ ተቋማት ዋነኛ ትኩረት በግብርናው ዘርፍ ላይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ማህበሩ በ2013 በጀት ዓመት 27ሺህ ሜትሪክ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 95 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታውቀዋል።