ቀጥታ፡

ሚዛኑን የሳተው አይኤምኤፍ

አዲስ አበባ፣ መስከረም04/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ዓመት የ10 ዓመት የልማት መሪ ዕቅድ ከመጽደቁ በፊት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ በመፍጠር መሪ ዕቅዱ የህዝብን ፍላጎት አሟልቶ የያዘ ሰነድ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል።

መሪ ዕቅዱ በተለይም ለማምጣት የታሰበውን የኢኮኖሚ እድገት በዜጎች ጓዳ እንዲደርስ የማድረግ መሰረታዊ ግብ መያዙ በተደጋጋሚ ተገልጿል፤ ሰነዱም በግልጽ አስቀምጦታል። የኢኮኖሚ እድገቱን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ብዝሃ የሆነ የእድገት ምንጭ እንዲኖራት ለማስቻል የተግባር እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

የመሪ ዕቅዱ ዋነኛ ትኩረት ድህነትን መቀነስ ብቻ ሳይሆን ተረጂነትን ማስወገድ መሆኑ ድንጋጤ የፈጠረባቸው ብዙዎች ናቸው። በተለይም ኢትዮጵያ የያዘችው የብልጽግና መንገድ ለአፍሪካ አገሮች ተምሳሌት በመሆን አህጉሩ ራስን የመቻል አዝማሚያ ውስጥ ከገባ በማንኪያ ሰጥተው በጭልፋ ለሚዘርፉት ሃይሎች ፈተና መጋረጡ አይቀሬ መሆኑ ስጋት አጭሮባቸዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የብልጽግና መንገድ ማደነቃቀፍ አስፈላጊና የግድ እንደሆነ በመወሰን የኢትዮጵያን ፈተና ማብዛት ላይ ትኩረት ተደርጎ መስራት ከተጀመረ ውሎ አድሯል። የለውጥ ጎዳና ላይ የምትገኘውን ኢትዮጵያን ከወዲሁ ማስቆም ካልተቻለ ነገሩ ሁሉ ‘ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም’ የሆነባቸው ሃይሎች ለኢትዮጵያ የተለያየ አጀንዳ በመስጠት የእድገት ጉዞውን ለመግታት የማይፈነቀል ድንጋይ እንደሌለ ማየት ይቻላል።

መገናኛ ብዙሃኑ፣ የእርዳታ ድርጅቶች፣ አገሮች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ የተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚሰሩ ተቋማት ሁሉ ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ እየሰሩ እንደሆነ ግልጽ ከወጣ ውሎ አድሯል።ከሰሞኑ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) በሚያወጣው የኢኮኖሚ እድገት መለኪያ ውስጥ እ.አ.አ ከ2022 እስከ 2026 ባለው የአምስት አመት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን እንደማያካትት ገልጿል።

ለዚህ እንደምክንያት አድርጎ ያቀረበው የእርግጠኝነት ማጣት እንደሆነ አመልክቷል።አይኤምኤፍ ያቀረበው ምክንያት ብዙም ውሃ የማይቋጥርና ሌሎች ምዕራባውያን አጋሮቹ በኢትዮጵያ የጀመሩት አገሪቱን ጫና ውስጥ የመክተት አሉታዊ ዘመቻ አንድ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ተቋሙ ኢትዮጵያን በተመለከተበት አይኑ የተመለከታቸው አገሮች ቢኖሩም ከኢትዮጵያ ጋር ፍጹም አብረው ሊመዘኑ አይችሉም፤ እይታው ‘ሊበሏት ያሰቧትን …’ የሚለውን አገራዊ ብሂል ያስታውሳል።የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሃዲዱን ይዞ በመጓዝ ላይ ቢሆንም ‘እኔ አውቅልሃለሁ’ የሚሉ ሃይሎች ምስክርነት ልንሰጥ አንችልም እያሉ ይገኛሉ።

በአገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያው መሰረት የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መጀመሩ ከዚህ ቀደም የአገሪቱን መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድን ጨምሮ በሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ሲገለጽ ቆይቷል።አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት በሁሉም አመላካቾች የሚለካበት ምቹ ሁኔታ አለ።

በዚህ ረገድ ከተቋማዊ ዝግጁነት ጀምሮ በሁሉም መስክ እድገቱን ለመለካት ብቻ ሳይሆን እድገቱን ለማረጋገጥ የሚቻልበት አገራዊ ዝግጁነት አለ።ይህ ሆኖ ሳለ በሴራ ትንተና የተካኑትና ተናበው የሚሰሩት ምዕራባውያን ለኢትዮጵያ አጀንዳ ለመስጠት ሙከራ ከማድረግ አልሰነፉም።

አይኤምኤፍ ለተቸገረበት የእድገት መለኪያ የፕላን ልማት ሚኒስትር ምላሽ ሊሰጠው ይችላል። ለዚህ ግን ተቋሙ ዘወትር የሚተችበትን ሚዛናዊነት የማጣት ጭምብሉን ማውለቅ ይጠበቅበታል።

ከዚህ ውጭ ግን አይኤምኤፍ ኢትዮጵያን የገለጸበት መንገድ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ከተፈጸሙ የፖለቲካ ፍላጎት ከተንጸባረቀባቸው የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እንዲሁም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ድርጊቶች የተለየ ሆኖ ሊታይ አይችልም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም