ቀጥታ፡

በህዝብ የተመረጠው መንግስት ለክልሉ ሰላምና የኑሮ ውድነት እንዲቀንስ በትኩረት መሰራት ይጠበቅበታል

ሐረር፤ ጥቅምት 3/2014 (ኢዜአ) በህዝብ የተመረጠው መንግስት በክልሉ ሰላም እንዲጎለብትና የኑሮ ውድነት እንዲቀንስ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚጠበቅበት በሐረሪ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመለከቱ።

በክልሉ በተካሄደው ምርጫ የህዝብ ይሁንታ  ካገኘው  ብልጽግና ፓርቲ ጋር በቅንጅት ለመስራት መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መካከል የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ተወካይ  አቶ አብዱልሃፊዝ አህመድ፤ በተካሄደው ምርጫ አሸናፊዎቹ ህዝብና በምርጫው የተሳተፉ ሁሉም ፓርቲዎች መሆናቸውን እንደሚያምኑ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ፓርቲያቸው  ህዝብን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች  ከመንግስት እና ከሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር  እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የተመረጠው የብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግስት በክልሉ  ሰላም እንዲሰፍንና  የኑሮ ውድነት እንዲቀንስ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን(አብን) አመራር አቶ ሔኖክ ሀይሉ በበኩላቸው፤  ህዝቡ የሚበጀውን በመምረጡ የመራጩን ውሳኔ  በፀጋ ተቀብለናል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ምርጫውን ካሸነፈው የብልጽግና ፓርቲ ከሚመራው መንግስት ጋር በመተባበር  ህዝብንና ሀገርን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

በህዝብ የተመረጠው መንግስትም በተለይም በክልሉ ፍትህ እንዲረጋገጥና ሰላም እንዲጎለብት  በትኩረት መስራት አለበት ነው ያሉት።

''ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ በመጠናቀቁ የምርጫውን ውጤት  በፀጋ ተቀብለናል'' ያሉት ደግሞ የሐረሪ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት አመራር አቶ ረምዚ አሊ ናቸው ፡፡

በቀጣይም ምርጫውን የህዝብ ይሁንታ ካገኘው  ብልፅግና ፓርቲ ከሚመራው መንግስት ጋር በቅንጅት ለመስራት መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፤ በተለይም መንግስት ስህተቶችን እንዲያርምና ጥንካሬዎቹን እንዲያጎለብት ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታወቀዋል።

የኢዜማ ፓርቲ አመራሩ አቶ አዝማች ጌጡ፤  የምርጫውን ውጤት በፀጋ መቀበላቸውን ጠቁመው፤ የተመረጠው መንግስት በተለይም በክልሉ የመጠጥ ውሃ ችግር እንዲቃለል፣ የቱሪዝም ዘርፉ እንዲጠናከርና የኑሮ ውድነት እንዲቀንስ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በሐረሪ  ክልል  መስከረም 20/2014 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ  ብልፅግና ፓርቲ በአብላጫ ድምፅ  የህዝብ ይሁንታ ማግኘቱን የኢትዮጵያ  ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀደም ብሎ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም