ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች የእጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን በምስራቅ አፍሪካ ውድድር ወደ ግማሽ ፍጻሜ አለፈ

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 በኡጋንዳ ርዕሰ መዲና ካምፓላ እየተካሄደ ባለው የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች የእጅ ኳስ ቡድን ኢትዮጵያን የወከለው ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፍ ችሏል። የዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀው ይህ ውድድር ከሶስት ቀናት በፊት መጀመሩ ይታወሳል። ኢትዮጵያ ከ18 እና 20 ዓመት በታች በሁለት ብሔራዊ ቡድኖች ተወክላለች። ትናንት ሶስተኛ ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የቡሩንዲ አቻውን 27 ለ 20 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ቡድኑ በምድቡ ያደረጋቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች በማሸነፍና አንደኛ በመሆን ወደ ግማሽ ፍጻሜ መግባቱን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ ለኢዜአ ገልጸዋል። ከ18 ዓመት በታች የእጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን ታንዛንያንና ኬንያን ማሸነፉ ይታወሳል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የእጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን ትናንት ከታንዛንያ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ 33 ለ 23 ማሸነፉን ጠቁመዋል። ቡድኑ በውድድሩ መክፈቻ ቀን ከጅቡቲ ጋር ጨዋታ ማድረግ የነበረበት ቢሆንም ጅቡቲ ከውድድሩ ራሷን በማግለሏ ምክንያት 10 ለባዶ በሆነ ውጤት በፎርፌ እንዲያሸንፍ መደረጉን አቶ ሞላ ገልጸዋል። ቀጣይ ጨዋታውን ዛሬ ከኬንያ ጋር እንደሚያካሂድ አክለዋል። የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች የእጅ ኳስ ውድድር ላይ አዘጋጇ ኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ብሩንዲ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ታንዛንያ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። ውድድሩ እስከ ግንቦት 12 ቀን 2010 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም