በሐረሪ ክልል የተካሄደው ምርጫ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው ሆኖ ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል የተካሄደው ምርጫ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው ሆኖ ተጠናቋል
ሐረር ፤ ጥቅምት 3/2014(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የተካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝብና ሀገር ያሸነፉበት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን የክልሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።
በክልሉ መስከረም 20/2014 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ ውጤት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ መሆኑን ተከትሎ የጋራ ምክር ቤቱ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የክልሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ መሀመድ ሀሰን አደም እንዳመለከቱት፤ በክልሉ መስከረም 20/ 2014 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ ከቅድመ እስከ ድህረ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው ሆኖ ተጠናቋል።
የምርጫው ውጤትም ህዝብና ሀገር ያሸነፉበት ነው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በክልሉ በህዝብ ይሁንታ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን ውጤት በማግኘቱ ለፓርቲው አመራሮችና አባላት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ቀጣይም ለሀገር ልማትና ብልጽግና ገንቢ ሀሳብ በመስጠት የነቃ ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አስታውቀዋል።
ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች ፣ለክልሉ ነዋሪዎች፣ ለፀጥታ አካላት፣ ለምርጫ ቦርድ፣ ለመገናኛ ብዙሃንና ሲቪክ ማህበራት ምስጋና አቅርበዋል።
ሰኔ 14 / 2013 ዓ.ም በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሲከናወን፤ በተለያዩ ምክንያቶች ባልተካሄደባቸው የሐረሪ፣ ሱማሌ እና ደቡብ ክልሎች ደግሞ መስከረም 20/ 2014 ዓ.ም መከናወኑንና ውጤቱንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።