ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር መዘጋጀት ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር መዘጋጀት ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር የአዲስ ተሿሚዎች ዋነኛ ተግባራቸው መሆን እንዳለበት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የኪነ-ጥበብና የሚዲያ ባለሙያዎች ተናገሩ።
የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋየ እና የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አርቲስት ደሣለኝ ሃይሉ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂዳ በህዝብ ተቀባይነት ያገኘ የመንግስት ምስረታ ማካሄዷን ገልጸዋል፡፡
በመንግስት ምስረታ ሂደትም ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከፍተኛ ቦታ ማግኘታቸው ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ ሂደት በአጭር ጊዜ ውስጥ ግቡን እንዲመታ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አርቲስት ደሣለኝ ሃይሉ እንዳለው አዲስ የተሾሙ ሚኒስትሮች የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ዋነኛ ተግባራቸው ሊሆን እንደሚገባ ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት በማስጠበቅ ሉዓላዊነቷ ተከብሮና በማንም ሊደፈር የማይችል አገር በመገንባት ላይም ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል ብሏል።
የዜጎች መፈናቀል፣ ሞትና የንብረት ውድመት እንዲቆም እንዲሁም ግጭቶች እንዲወገዱ ከከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ብዙ ስራ ይጠይቃል ነው ያለው።
የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ፤ በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ሂደት በበርካታ ተግዳሮቶች ታጅቦም ቢሆን ስኬቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የለውጥ ሂደቱ የታሰበለት ዓላማ ተሳክቶ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ ሁላችንም የሚጠበቅብንን ሃላፊነት ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
አዲስ ተሿሚዎች ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ህዝቡን ተጠቃሚ የማድረግ ታላቅ ሃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ከውጭም ሆነ ከውስጥ ሆነው የኢትዮጵያን ህልውና የሚገዳደሩ አካላትን መመከትም እንዲሁ።
አርቲስት ደሣለኝ ሃይሉም የኑሮ ውድነትን እና የስራ አጥነት ችግሮችንም መፈታት የአዲስ ተሿሚዎች ትኩረት ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡
መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ አዲስ የመንግስት ምስረታ እውን መሆኑ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሚኒስትሮችን ለማሾም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት አዲስ ተሿሚዎች ሌብነትና ልመናን ማጥፋት እንዲሁም በአካባቢ ሳይታጠሩ ኢትዮጵያን ለመምራት ተዘጋጁ በማለት ማሳሰባቸው ይታወሳል።