የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ለ150 ዓይነስውራን ዘመናዊ አጋዥ መሳሪያ ሰጠ

112

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2014(ኢዜአ) የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ለ150 ዓይነስውራን "ኦርካም ማይ አይ" የተሰኘ በዓይን መነፅር ላይ የሚገጠም ዘመናዊ አጋዥ መሳሪያ አበርክቷል።

መሳሪያው ከእስራኤል በመጡ ባለሙያዎች አማካኝነት ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ ዓይነስውራን ከስልጠና ጋር ነው ተሰጥቷቸዋል።

"ኦርካም ማይ አይ" የተሰኘው ዘመናዊ መሳሪያ በመነጽር ላይ የሚገጠምና መፅሃፍት፣ ጋዜጣ ወይንም መጽሄት፤ የመንገድ ምልክቶች፣ ሞባይል እንዲሁም ስክሪን ላይ የተጻፉ ፅሁፎችን የሚያነብ እንደሆነ ተገልጿል።

በገበያ ቦታ ወይም በሱፐር ማርኬት ውስጥ ተጠቃሚው በቀላሉ እንዲገበያይ የሚረዳው እንደሆነም እንዲሁ።

መሳሪያው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የተገጠመለት ሲሆን፤ ተጠቃሚው ይበልጥ እየተገለገለበት በሄደ ቁጥር የመሳሪያው እገዛ እያደገ የሚሄድ መሆኑም ተገልጿል።

ዘመናዊ አጋዥ መሣሪያውን ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለዓይነ ስውራኑ ሰጥተዋል።

ቀዳማዊት እመቤቷ ጽህፈት ቤታቸው በተለይ አካል ጉዳተኞች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አንስተው፤ ማየት የተሳናቸው የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎችን በማየቴ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።

በቀጣይም ድጋፉን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው 300 ዓይነ ስውራንን ለመቀበል ታስቦ እየተገነባ ያለው አዳሪ ትምህርት ቤት በሚቀጥለው ዓመት አገልግሎት እንደሚጀምር ይጠበቃል ብለዋል።

የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎች በበኩላቸው እንዲህ ያለው በጎ ምግባር የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቴክኖሎጂው የተሻለ እንደሚታገዙ እምነታቸውን ገልጸዋል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ላደረገላቸውድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም