ዳያስፖራው በሁለት ወራት ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ 122 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው በሁለት ወራት ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ 122 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል
ጥቅምት 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በሁለት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል 122 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት አባላት በአዲስ አበባ ቤተል አካባቢ በሚገኘው ሕዳሴ ፓርክ ቀደም ሲል የተተከሉ ችግኞች ተንከባክበዋል።
የጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ አብርሃም ዳያስፖራው ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገው ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ እስካሁን ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት አቶ ሃይሉ ባለፉት ሐምሌና ነሐሴ ወራት ብቻ 122 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ከዳያስፖራው መገኘቱን ተናግረዋል።
ከዳያስፖራ አባላቱ መካከል አቶ ፍቃዱ ተረፈ የውጭና የውስጥ ሃይሎች ኢትዮጵያ እንዳትለማ ጫና ለመፍጠር እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
ይህንን እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ለሚሰሩ ሃይሎች ዕድል ባለመስጠት የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ በእውቀታቸውና በገንዘብ የሚያደርጉትን ድጋፍ ከምንጊዜውም በላይ እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
ወይዘሮ ኢትዮጵያ አለማየሁ በበኩላቸው የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ ከአላቸው ላይ በመቀነስና ድጋፍ በማሰባሰብ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለማሻገር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በመገንባት፣ በልማትና በትውልድ ቀረጻ ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት በመስከረም 2013 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችን የያዘ ነው።
የምክር ቤቱ አባላት "እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ የፍቅር ጉዞ" በሚል ከአዲሱ ዓመት መጀመሪያ አንስቶ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛል፤ አባላቱ ለአገር መከላከያ ሠራዊት ደም የለገሱ ሲሆን ከትናንት በስቲያም የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለበትን ደረጃ ጎብኝተዋል።