ቀጥታ፡

አየር መንገዱ 'ሳብሬ' ከተሰኘ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር አብሮ መሥራት የሚያስችለውን ሥምምነት አደሰ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ "ሳብሬ" ከተሰኘ የሶፍትዌርና የቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያ ጋር ለመጪው ሰባት ዓመታት አብሮ መሥራት የሚያስችለውን የ110 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሥምምነት አደሰ።

በሥምምነቱም መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ "ሳብሬ-ሶኒክ" የተሰኘውን የሳብሬ የመንገደኞች አገልግሎት ሥርዓት ቴክኖሎጂ መጠቀሙን ይቀጥላል ተብሏል።

ይህም አየር መንገዱ የሽያጭና የአገልግሎት ሥርዓትን ለማዘመን፣ የገቢ መጠን ለመጨመርና ለመንገደኞችም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

ከዚህ በተጨማሪም የሳብሬ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት ለአየር መንገዱ ተሳፋሪዎች በመረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ ለማሳለፍ እንደሚረዳም ኤር 101 በድረ-ገጹ አስነብቧል።

የሳብሬ ኮርፖሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ዲኖ ጌልመቲ እንዳሉት "የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ ውስጥ ሆኖም በአቬሽን ኢንዱስትሪው ስኬት ማስመዝገቡን ቀጥሏል" ብለዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የአየር መንገዶችን ተወዳዳሪነትና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፍላጎትን እያቀላጠፈ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ግዙፉ የአፍሪካ የአቬዬሽን ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድም ተለዋዋጭ እየሆነ ከመጣው ዓለም ጋር እራሱን እያጣጣመ አገልግሎቱን እያጠናከረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሥምምነቱም አየር መንገዱ በገበያ ፍላጎትና ውድድር ላይ የተመሠረተ የዋጋ እና አገልግሎት አሰጣጥ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ ተወዳዳሪና ተጠቃሚነቱን ያሳድጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፤ “ጠንካራና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መኖሩ ለአየር መንገዱ የስኬት ታሪክ ቁልፍ ሚና ይጫወታል” ብለዋል።

የሳብሬ የደህንነት ቴክኖሎጂም አየር መንገዱ ከአዲሱ የዓለም ገጽታ ጋር በፍጥነት ለመላመድ እንደሚረዳው ገልጸዋል።

የጉዞ ኢንዳስትሪው ማገገም ሲጀምርም በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋና ዘመናዊ ተግባራትን በማከናወን ትርፋማነትና እድገት ላይ ያተኮረ ወሳኝ ሥራዎችን ለመሥራት እንደሚያስችል አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም