በምንጓዝበት የዓለም ሃገራት ሁሉ የኢትዮጵያን እውነት በማስረዳት የበኩላችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
በምንጓዝበት የዓለም ሃገራት ሁሉ የኢትዮጵያን እውነት በማስረዳት የበኩላችንን እንወጣለን
ደሴ ፤ ጥቅምት 2/2014 (ኢዜአ) በሚጓዙባቸው ሀገራት ሁሉ የኢትዮጵያን እውነትና አሁናዊ ሁኔታ ለዓለም ህዝብ በማስረዳት የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል የድርሻቸውን እንደሚወጡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች ገለጹ፡፡
የአየር መንገዱ አብራሪዎች በአሸባሪው ህወሃት ተፈናቅለው ደሴና ኮምቦልቻ ከተማ ለተጠለሉ ወገኖች ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ዱቄትና ጥሬ ገንዘብ አበረከቱ፡፡
ከአብራሪዎች መካከል ካፒቴን በህሩዲን አብዱ እንዳመለከቱት፤ የዓለም ህዝብ በተሳሳተና በተዛባ መረጃ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና እያሳደረ ይገኛል።
ይህን ለመከላከልም ጠንካራ አንድነት ፈጥሮ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በግላቸውም ለስራ ጉዳይ በሚሄድባቸው ሀገራት ሁሉ እውነተኛውንና አሁናዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ ለዓለም ህዝብ በማስረዳት የውጭ ጫናውን ለመከላከል እንደሚጥሩ ተናግረዋል።
እስካሁንም የኢትዮጵያን ባህል፣ እሴትና አብሮነት በተለያየ መንገድ በመግለጽ እውነቱን እንዲረዱ ጥረት ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ ዳር ድንበሯ የተከበረች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁላችንም የምንችለውን ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ጣልቃ ገብነቱን በጋራ እየተከላከልን ተጎጂ ወገኖችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋምም እንሰራለን ያሉት ካፒቴኑ ፤ በተነሳሽነት ከራሳቸው ያሰባሰቡትን ዛሬ በአካል ተገኝተው በማበርከታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌላው ካፒቴን ጓዴ ተሾመ ፤ ሁሉም በተሰማራበት የሙያ ዘርፍ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ እውነታውን ለዓለም ማስረዳትና የውጭ ጣልቃ ገብነቱን መከላከል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
እኛም ለበረራ በምንሄድባቸው ሀገራት ሁሉ የኢትዮጵያን እውነትና ትክክለኛ ገጽታ በማስረዳት ጣልቃ ገብነቱን ከመከላከል ባለፈ ባህልና እሴቶቻችንንም ተገንዝበው ወዳጅነታቸውን እንዲቀጥሉ የሚጠበቅብንን እናደርጋለን ብለዋል፡፡
''በአየር መንገዱ ስንሰራ የኢትዮጵያ አምባሳደርና ወኪሎች ነን'' ያሉት ካፒቴኑ፤ ትክክለኛውን በማስረዳት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡
ካለችን ጊዜ አጣበን በ15 ቀን ከአየር መንገዱ አብራሪዎች ባሰባሰብነው ገንዘብ ለተፈናቃይ ወገኖች ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ዱቄትና ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አድርገናል ያሉት ደግሞ የድጋፉ አስተባባሪ ካፒቴን አህመድ አባድር ናቸው፡፡
ከድጋፉ መካከል 500 ኩንታል ዱቄት፣ ለወላድ፣ ነፍሰ ጡር እናቶችና አቅመ ደካሞች ደግሞ በጥሬ ገንዘብ የተበረከተው ይገኙበታል።
ጣልቃ ገብነቱን ከመከላከል ባለፈ ተፈናቃይ ወገኖችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋምም የአየር መንገዱ አብራሪዎች የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ዝግጁ ናቸው ብለዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ማሩ እንዳሉት፤ የአየር መንገዱ አብራሪዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ያደረጉት ድጋፍ የሚበረታታ ነው፡፡
መንግስት ህብረተሰቡንና ተቋማትን አስተባብሮ የዕለት ደራሽ ምግብ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተው፤ ካለው ተፈናቃይ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ሁሉም የሚችለውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በአሸባሪው ህወሃት ተፈናቅለው ደሴና ኮምቦልቻ አካባቢ የተጠለሉ ወገኖች ቁጥር ከ350 ሺህ ማለፉንም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች ድጋፉ ለተጎጂዎቹ እንዲደርስ ካስረከቡ በኋላ ደሴና ኮምቦልቻ ከተማ የተጠለሉ ተፈናቃይ ወገኖችን ተዘዋውረው በመጠየቅ አበረታተዋል።