ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጀስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ በጋራ ለመስራት ተፈራረሙ

ጥቅምት 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጀስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የስራ ውል ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱ በዋናነት ዩኒቨርሲቲው እና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጀስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ የባቡጋያ ማሪታይምና ሎጀስቲክ አካዳሚ የትምህርትና ሙያ ስልጠና አቅም ለማሳደግ በጋራ እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው፡፡

ስምምነቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጀስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ ተፈራርመዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በዚህን ወቅት ዩኒቨርሲቲው የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጀስትክ አካዳሚን አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ስልጠና ለመስጠት ሙሉ አቅምና ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በኢንጅነሪንግ፣ ቢዝነስ፣ ሎጀስቲክስ እና ሌሎች የትምህርት ዘርፎች ላይ አቅምን ለማሳደግ የሚረዱ ስልጠናዎችን የመስጠት አቅም እንዳለውም ጨምረው ገልጸዋል።

አጫጭር ስልጠናዎችን ጨምሮ በመጀመሪያና ሁለተኛ ድግሪ ስልጠናዎችን በመስጠት ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚሰራም ነው የገለጹት።  

ስምምነቱ አካዳሚው በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያግዘውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ሎጀስቲክ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ፤ የማሪታይምና ሎጀስቲክ አገልግሎት አካዳሚን በሙሉ አቅም በመጠቀም ረገድ ክፍተት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ስምምነቱ በዘርፉ ያለውን ክፍተት በመሙላት ብቁ የማሪታይምና ሎጀስቲክ ባለሙያዎችን በማፍራት  የስራ እድል ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የስራ ገበያ የሚፈልገውን ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ኢትዮጵያ ከዘርፉ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወትም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም