አዲሱ መንግስት የሀገርን ሉዓላዊነት ባስጠበቀ መልኩ የውጭ ዲፕሎማሲን ማጠናከር ቀዳሚ ተግባሩ መሆን አለበት - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ መንግስት የሀገርን ሉዓላዊነት ባስጠበቀ መልኩ የውጭ ዲፕሎማሲን ማጠናከር ቀዳሚ ተግባሩ መሆን አለበት
አዳማ፤ ጥቅምት 2/2014(ኢዜአ) አዲሱ መንግስት የሀገርን ሉዓላዊነት ባስጠበቀ መልኩ የውስጥ አንድነትንና የውጭ ዲፕሎማሲን ማጠናከር ቀዳሚ ተግባሩ መሆን እንዳለበት ተመለከተ።
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንደገለጹት፤ ሀገሪቱ በብዙ ፈተና ውስጥ አልፋ ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ፣ ለሀገር ልማትና ዕድገት የሚመጥን አዲስ መንግስት መመስረት ችላለች።
በዩኒቨርሲቲው የአመራርና ለውጥ አስተዳደር መምህር ባልቻ ከበደ ፤ሀገሪቱ የመሰረተችው መንግስት በብልሃት፣ ብስለትና ቆራጥ አመራር ሰጪነት እውን መሆኑን ተናግረዋል።
አዲሱ መንግስት የሀገርን ሉዓላዊነት ባስጠበቀና ባስከበረ መልኩ የውስጥ አንድነትንና የውጭ ዲፕሎማሲን ማጠናከር ቀዳሚ ተግባሩ መሆን አለበት ነው ያሉት።
“በተለይ የሀገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እከልነትን በጠበቀ መልኩ የውስጥ ጥንካሬያችን ማጎልበት ላይ በሙሉ አቅሙ መስራት ይጠበቅበታል” ብለዋል።
በአንድነት ውስጥ ባለብዙ ማንነትና ልዩነት አለንያሉት ምሁሩ ፤ይሄን ውበታችን ለሀገራችን አንድነት መጠናከር ፣ ለለውጥና ዕድገት ልንጠቀምበት እንደሚገባ አመልክተዋል።
“ኢትዮጵያ በልማትና በእድገት ቀና እንድትል የማይፈልጉ ጠላቶችን መመከት የምንችለው በውስጥ አንድነታችን ማጠናከር ላይ ተባብረን ስንሰራ ነው” ብለዋል።
እንደምሁሩ ገለጻ፤ የመንግስት ምስረታው የተለያዩ ሃሳቦችንና የፖለቲካ ልዩነቶችን አንድ ላይ በማምጣትሀገርን ለማሻገር የሚያስችል አዲስ ምዕራፍ የታየበት ነው።
ይህም ሀገራዊ አንድነትን ከማጠናከር አንፃር የላቀ ሚና ያለው ጅምር እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
የለውጥ ሃይሉ የውስጥ ሴረኞችና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የከፈቱብንን ጦርነት ተቋቋሞ ጠንካራ መንግስት መመስረት መቻሉ አንድ ሆነን ስንቆም የሚቋቋመን የሌለ መሆኑን ያመለክታልያሉት ደግሞ ሌላው የዩኒቨርሲቲው ምሁር አስፋው ደሴ ናቸው።
በሀገሪተ የረዥም ጊዜ ታሪክ እንደሚታወቀው የሚመሰረተው መንግስት በምርጫ ማግስት ልዩነት ያላቸው ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎችን አሳዶ ማሰርና ሀገር ጥለው እንዲሰደዱ ማደረግ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአዲሱ መንግስት ምስረታ ገዥው እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠላት የመተያየትና የሰዶ ማሳደድ ምዕረፍ በመዝጋት ሀገርን በጋራ ለመገንባት አዲስ በር የከፈተ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት የውጭ ተፅዕኖን በመቋቋም የህዳሴ ግድብ ፕሮጆክት ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ማካሄድ፣ ምርጫ በማካሄድ መንግስት በመመስረት ሀገርን ከብተና መታደጉ ትልቅ እውቅና የሚሰጠውና ኢትዮጵያ ማሸነፏን የሚያረጋግጥ ስኬት ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች መንግስት የያዘውን እቅድ ለማሳካት የሚያግዙ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ለማከናወን ወደ ስራ መግባቱም ተመልክቷል።
ከኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በአመራርና የለውጥ አስተዳደር በሁለተኛ ድግሪ የተመረቁት ኡጆንግ ዶም ቻምብ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የአጎራባች ክልሎችን የሰው ሃይል የማስፈፀም አቅም ለመገንባት ለጋምቤላ ክልልበሰጠው የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የተሰጠን ዕድል ህብረብሔራዊ ወንድማማችነትን ከማጠናከር ባለፈ አብሮ መልማት፣ ማደግና መለውጥ አንዱ ማሳያ ነው ያሉት።
“አዲሱ መንግስት ለውጭ ጫና ሳይንበረከክ ይዞ የመጣውን አሸናፊነት በማስቀጠል የሀገር ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ አለበት ብለዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ገዥው ፓርቲ በሀገር አንድነትና በዜጎች ሰላም ማስጠበቅ ላይ እኩል እንዲሰሩ እድል የሰጠ የመንግስት አደረጃጀት መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።