ቀጥታ፡

የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለ39ኛው የህብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ አዲስ አበባ እየገቡ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 2/2014(ኢዜአ) የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል።

የሕብረቱ ኮሚሽን የሚያዘጋጀው የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ጥቅምት 4 እና 5 ቀን 2014 ዓ.ም በአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል።

በስብሰባው ለመሳተፍ የላይቤሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲ-ማክስዌል ሳህ ኬማያ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የፕሮቶኮል ዋና ሹም አቶ ፈይሰል ዓሊ እና ሌሎች የሚኒስቴሩ የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ዲ-ማክስዌል ሳህ ኬማያ ከጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ የላይቤሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው እየሰሩ ይገኛል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ከመሾማቸው በፊት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የላይቤሪያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው አገልግለዋል።

በ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የሕብረቱ 55 አባል አገራት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የምክር ቤቱ ስብሰባ የአገራት መሪዎች፣ የአፍሪካ ሕብረት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማኀበረሰብ ተቋማትና በሕብረቱ ስር የሚገኙ ተቋማት የሚያደርጉት በሶስተኛው አጋማሽ ዓመት ለሚያደርጉት ጥምር ውይይት አጀንዳዎች የሚቀርቡበት ነው።

በዚሁ መሰረት 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

በመስከረም 2014 ዓ.ም የተካሄደው 42ኛው የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ ተወካይ ኮሚቴ ስብሰባና የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል የአፈጻጸም ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድም የአፍሪካ ሕብረት አስታውቋል።

ምክር ቤቱ "የተመጣጠነ ምግብና የምግብ ዋስትና" የአፍሪካ ሕብረት እ.አ.አ የ2022 መሪ ቃል ሆኖ እንዲሰየም በቀረበው የመነሻ ሃሳብ ላይ ይወያያል።

የስራ አስፈጸሚ ምክር ቤቱ በስሩ የሚገኙ የተለያዩ ኮሚቴዎች፣ ንዑስ ኮሚቴዎችና የአጀንዳ 2063 አፈጻጸምን አስመልክቶ የሚቀርቡ ሪፖርቶችን በማድመጥ ምክክር እንደሚያደርግም ይጠበቃል።

በስብሰባው በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ስር ለሚገኙ ሁለት ዘርፎች የኮሚሽነሮች እንዲሁም የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት ምርጫ ይካሄዳል።

በተጨማሪም የሠብዓዊና የዜጎች መብቶች ኮሚሽንና የአፍሪካ ሕብረት የፀረ-ሙስና አማካሪ ቦርድ በተመሳሳይ የአራት አባላት ምርጫ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በስብሰባው መክፈቻ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት፣ የሕብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የወቅቱ ሰብሳቢና የዴሞክራቲክ ኮንጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራይሞንድ ንቱንጋሙሎንጎ፣ የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ቬራ ሶንግዌ ንግግር እንደሚያደርጉ የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።

የአፍሪካ አገራት መሪዎች የሚሳተፉበት የአፍሪካ ሕብረት፣ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ተቋማትና በአፍሪካ ሕብረት ስር የሚገኙ ተቋማት የሚያደርጉት ሶስተኛው የአጋማሽ ዓመት ጥምር ውይይት ጥቅምት 6 ቀን 2014 ዓ.ም በበይነ መረብ እንደሚካሄድ የአፍሪካ ሕብረት አስታውቋል።

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጸሚ ምክር ቤት ስብሰባና ሶስተኛ የአጋማሽ ዓመት ጥምር ውይይት በቻድ መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በአገሪቷ ባለው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም