የውጭ ጫናን ለመቋቋም ከወዳጅ ሀገራትና ተቋማት ጋር መተማመንን መሰረት ያደረገ ግንኙነትን ማጠናከር ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጫናን ለመቋቋም ከወዳጅ ሀገራትና ተቋማት ጋር መተማመንን መሰረት ያደረገ ግንኙነትን ማጠናከር ያስፈልጋል
ዲላ፤ ጥቅምት 1/2014 (ኢዜአ) የውጭ ጫናን ለመቋቋም ከወዳጅ ሀገራትና አለም አቀፍ ተቋማት ጋር መተማመንን መሰረት ያደረገ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የህግ ምሁራን አመለከቱ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዲላ ዩንቨርስቲ ምሁራን እንዳሉት፤ የግንኙነቱ መጠናከር ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትንና የእርዳታ አቅርቦትን ምክንያት አድርጎ የሚመጣባትን ጫና ለመቋቋም ያግዛል።
በዩኒቨርስቲው የህግ ምሁር ሄኖክ አሻግሬ፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ በተደጋጋሚ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት መታየቱ በራሱ ችግር ባይሆንም ጉዳዩ የሚነሳበት አግባብ ፍትሃዊነት የጎደለውና ሉዓላዊነትን የሚጋፋ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት።
የድርጅቱ መቋቋሚያ አዋጅ አባል ሀገራት የሰብዓዊ መብትን በማክበርና ማስከበር እንዲሁም ተባባሪ የመሆን ግዴታ ቢያስቀምጥም የሀገር ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ እንደማይገባ ጠቁመዋል።
አንድ ሀገር በውስጥ ጉዳዬ ገብተዋል ብላ ስታምን የድርጅቱ ሰራተኞችን ይቅርና ዲፕሎማቶች እንኳን የማባረር መብት እንዳላት በቬና የግንኝነት ቃልኪዳን ከስምምነት መደረሱን አስረድተዋል።
''ማህበራዊ ቀውሱን ተገን አደርገው የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸው ግልጽ ነው'' ያሉት ምሁሩ፤ ይህንን ከመከላከል በተጓዳኝ ለአለም አቀፍ ጫናዎች በር የሚከፍቱ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በህወሓት የሽብር ቡድን የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በተደራጀ መንገድ መረጃ በመያዝ ማጋለጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አለም አቀፍ ተቋማትና ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ አገዥ ሃይል ሆነው መቀጠላቸው ከዲፕሎማሲው በሻገር ለምጣኔ ሃብቱም አስተዋጾኦ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ከወዳጅ ሀገራትና አለም አቀፍ ተቋማት ጋር መተማመንን መሰረት ያደረገ ግንኝነት እንዲኖር ትኩረት አድርጎ በመስራት ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የአለም አቀፍ ህግ ምሁር አማኑኤል ታደሴ በበኩላቸው፤ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት፣ከህግ ማስከበርና ከህልውና ዘመቻ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ የተከፈተው አለም አቀፍ ጫና ዓላማው ጣልቃ መግባት መሆኑን አስረድተዋል።
የህወሓት የሽብር ቡድን በኤርትራ ላይ የፈጸመው ትንኮሳ በማሳያነት ያነሱት ምሁሩ፤ ቡድኑ የከፈተው ጦርነት የውስጥ ጸጥታና የሰላም ብሎም የአፍሪካ ቀንድ ስጋት ነው ያሉት።
ሆኖም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጨምሮ አንዳንድ አለም አቀፍ ተቋማት ጉዳዩን የሚያዩበት መነጽር የተዛባና በበቂ መረጀ ያልተደገፈ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ድርጊት ተቋማቱ ከተመሰረቱበት መርህ በተቃራኒው መቆማቸውን በግልጽ የሚያሳይ እንደሆነ ነው ያመላከቱት።
በሰብዓዊ መብት ጥበቃና እርዳታ ሽፋን የሚደረግ ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ጫናዎችን ለመቋቋም በመረጃና ማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ዲፕሎማሳዊ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በተለይ ከኢትዮጵያ ጥቅም ጎን ከቆሙ ወዳጅ ሀገራት ጋር በትብብር ከመስራት ባለፈ ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር መተማመንን መሰረት ያደረገ ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰባት ሰራተኞች የተመደቡበትን ሰብዓዊ አገልግሎት በገለልተኛነት፣ በሰብዓዊነትና በነጻነት መሥራት ሲገባቸው ሀሰተኛና የተዛባ መረጃ በማስተላለፍ፣ የጦር መሣሪያ በማቀበልና በሌሎች የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሳተፍ ለአሸባሪው የህወሓት ቡድን ሲሰሩ በመገኘታቸው በ72 ሰዓት ውስጥ ሀገራችንን ለቀው እንዲወጡ መደረጉ ይታወቃል።